ሁለተኛው የቻይና ተንሳፋፊ የስለላ ፊኛ በደቡብ አሜሪካ መታየቱ ተገለጸ
አሜሪካ ከቀናት በፊት ወደ አየር ክልሌ ገብቷል ያለችውን ተመሳሳይ ፊኛ መትታ መጣሏ ይታወሳል
ቻይና በበኩሏ ተነሳፋፊ ፊኛው በአሜሪካ መመታቱን አውግዛለች
ሁለተኛው የቻይና ተንሳፋፊ የስለላ ፊኛ በደቡብ አሜሪካ መታየቱ ተገለጸ፡፡
ከሰሞኑ ንብረትነቱ የቻይና የሆነ ተንሳፋፊ የስለላ ፊኛ ወደ አሜሪካ እና ካናዳ ከተሞች መግባቱን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል ውጥረት ነግሶ ቆይቷል፡፡
በዚህ ተናሳፋፊ ፊኛ ምክንያትም ቻይናን ሊጎበኙ የነበሩት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጉዟቸውን ወደሌላ ጊዜ ለማዛወር ተገደዋል፡፡
ዋሸንግተን ወደ አየር ክልሏ የገባው የቻይና ተናሳፋፊ ፊኛን ተኩሳ መትታ የጣለች ሲሆን ድርጊቱ በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንደተፈጸመ ሮይተርስ አስነብቧል፡፡
ቻይና በበኩሏ ሰው አልባ እና መረጃዎችን ለመሰብሰብ ያለመ ተንሳፋፊ ፊኛ ወደ አየር መላኳን ገልጻ በአሜሪካ መመታቱን አውግዛለች፡፡
የአሜሪካ ሪፐብሊካን ፖለቲከኞች በበኩላቸው የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳድር ተነሳፋፊ ፊኛው ለቀናት በአሜሪካ አየር ክልል ውስጥ ከገባ በኋላ ለቀናት መጠበቃቸውን ተችተዋል፡፡
አሁን ደግሞ ተመሳሳይ የሆነ የስለላ ተንሳፋፊ ፊኛ በደቡብ አሜሪካዊቷ ኮሎምቢያ አየር ክልል ውስጥ የቻይና ንብረት የሖነ ፊኛ መገኘቱ ተገልጿል፡፡
የኮሎምቢያ መንግስት ጉዳዩን እየተከታተለ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የተባለፊ ተንሳፋፊ ፊኛ የእሷ መሆኑን እና ባልታወቀ ምክንያት ወደ ደቡብ አሜሪካ እና ካሪቢያን ሀገራት መጓዙን ጠቅሳለች፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሊዮልድ ኦስቲን በቻይና ድርጊት መበሳጨታቸውን ገልጸው ቤጂንግ በተንሳፋፊ ፊኛዎች አማካኝነት የአሜሪካንን ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን ለመሰለል ሞክራለች ብለዋል፡፡
ቻይና በበኩሏ ፊኛዎቹ መደበኛ መረጃዎችን ለማግኘት መሰማራታቸውን ገልጻ የአሜሪካ ድርጊት ግን ዓለም አቀፍ መደበኛ ድርጊቶችን የሚጎዳ እንደሆነ አስታውቃለች፡፡