ስሪላንካ በወረቀት እጥረት ምክንያት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ተማሪዎቿ ልትሰጥ የነበረውን ፈተና አራዘመች
የደቡብ እስያዋ ስሪላንካ ኢኮኖሚዋ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተፈተነ ይገኛል
ስሪላንካ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎቿን ለመፈተን ፕሮግራም ይዛ ነበር
በህትመት ወረቀቶች እጥረት ምክንያት ስሪላንካ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ተማሪዎቿ ልትሰጥ የነበረውን ፈተና ሰረዘች፡፡
የደቡብ እስያዋ ስሪላንካ በነገው ዕለት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎቿ ፈተና ላይ እንደሚቀመጡ አስቀድማ ቀነ ቀጠሮ የቆረጠች ቢሆንም ፈተናው ላልተወሰነ ሌላ ጊዜ መተላለፉን አስታውቃለች፡፡
አገሪቱ ፈተናውን ያራዘመቸው በህትመት ወረቀት እጥረት ምክንያት መሆኑን ተነግሯል፡፡ ስሪላንካ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት የገጠማት ሲሆን የፈተናው መራዘምም የዚሁ አካል ነው፡፡
22 ሚሊዮን ህዝብ ብዛት ያላት ሲሪላንካ ለፈተና የሚጠቅሙ ወረቀት እና ሌሎች ተያያዥ ምርቶችን ከውጭ አገራት በመግዛት ወደ አገር ውስጥ ታስገባ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማጋጠሙ ፈተናውን ማራዘም ግድ ብሏታል፡፡
የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት ከፈረንጆቹ 1948 ጀምሮ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት ግን ችግሩን ለመቋቋም መቸገሯ ነው የተገለጸው፡፡ ለዜጎቿ ምግብ፣ ነዳጅ እና መድሃኒቶችን መሰል መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማቅረብ ተቸግራለችም፡፡
ለአንድ ዓመት 6 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ በጀት የሚያስፈልጋት ቢሆንም አሁን ላይ የአገሪቱ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ መጠን 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው ተብሏል፡፡
በዚህም የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ደጅ ለመጥናት ተገዳለች እንደ አረብ ኒውስ ዘገባ፡፡