ስሪላንካዊቷ በኢትዮጵያ የመብት ጥሰቶች ለማጣራት የተቋቋመው የኤክስፐርቶች ኮሚሽን አባል ሆነው ተሾሙ
ስሪላንካዊቷ ራዲካ ኩማራስዋሚን ለኮሚሽኑ የተሸሙት በተሰናባቿ ፋቱ ቤንሱዳ ምትክ ነው
መርማሪ ቡድኑ በነገው እለት ሰኔ30 ቀን 2022 ለሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የመጀመሪያው የቃል ሪፖርት ያቀርባል
የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ስሪላንካዊቷ ራዲካ ኩማራስዋሚን በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የተባሉትን የመብት ጥሰቶች ለማጣራት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን አባል አድርጎ መሾሙ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ፌዴሪኮ ቪሌጋስ አስታወቁ፡፡
በዚህም መሰረት የቀድሞው የሲሪላንካ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሊቀመንበር ኩማራስዋሚ ፤ ባሳለፍነው በመጋቢት 2 ቀን 2022 በሰብዓዊ መብት መርማሪ አካል ውስጥ እንዲያገለግሉ ከተሾሙት ኬንያዊቷ ካአሪ ቤቲ ሙሩንጊ (ሊቀመንበር) እና አሜሪካዊው ስቲቨን ራትነር ጋር የሚቀላቀሉ ይሆናል ፡፡
መቀመጫውን ጄኔቫ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ከህዳር 3 ቀን 2020 ጀመሮ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎችን እና የመብት ጥሰቶችን ለማጣራት ስልጣን ያለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን ፤ እንደፈረንጆቹ ታህሳስ 17 ቀን 2021 ማቋቋሙ መሚታወስ ነው፡፡
በተቋቋመው ዓለም አቀፍ የኤክስፐርቶች መርማሪ ቡዱን ውስጥ የቀድሞ የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዓቃቤ ህግ ፋቱ ቤንሱዳ፣ ኬንያዊቷ ጠበቃና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ እና በሚቺጋን የሕግ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት አሜሪካዊ ስቲቨን ራትነር የኮሚሽኑ አባል መሾማማቸውም ጭምር የሚታወቅ ነው፡
ይሁን እንጅ ውስጥ የቀድሞ የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዓቃቤ ህግ ፋቱ ቤንሱዳ ባላፍነው ሰኔ 8 ቀን 2022 ከኮሚሽኑ ስለለቀቁ፤ ምክር ቤቱ አዲስ አባል ማካተት ግድ ሆኖበታል፡፡
ለዚህም በተሰናባቿ ፋቱ ቤንሱዳ ምትክ ስሪላንካዊቷ ራዲካ ኩማራስዋሚን በትናንትነው እለት አዲስ አባል አድርጎ ሾሟል፡፡
ፋቱ ቤንሱዳ ከአባልነት የተሰናበቱት በዩናይትድ ኪንግደም የጋምቢያ ከፍተኛ ኮሚሽነር ሆነው በመሾማቸው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
አዲሷ ተሿሚ ኩማራስዋሚ በሀገራቸው እና በዓለም አቀፍ መድረኮች በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ የሰብአዊ መብት ጠበቃ፣ ኤክስፐርት እና ተሟጋች በመሆን የረዥም ዓመታት ልምድ ያካበቱ ናቸው።
ኩማራስዋሚ እንደፈረንጆቹ ከ 2017 እስከ 2019 በምያንማር የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተፈጠረን ቀውስ ተከትሎ የገለልተኛ ዓለም አቀፍ እውነታ ፍለጋ ተልዕኮ አባል እንዲሁም ከ2006 እስከ 2012 በነበሩ ጊዝያት መሰል ግጭቶች ከማጣራትና ከህጻናት ጋር በተያያዘ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ ልዩ ተወካይ ሆነው ያገለገሉ ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የተባሉትን የመብት ጥሰቶች ለማጣራት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን ፤ አስከሁን የሰራውን ስራ በተመለከተ በነገው እለት ሰኔ30 ቀን 2022 ለሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የቃል ሪፖርት ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኮሚሽኑ ለምክር ቤቱ ከሚያቀርበው የቃል ሪፖርት በተጨማሪ በዚህ አመት መጨረሻ ላይ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ አጠቃላይ የጽሁፍ ሪፖርት ለማቅረብ ቀጠሮ ይዟል።