ልጆች ከፍተኛ የማሰላሰል አቅም ይዘው እንዲወለዱ የሚያደርገው አዲስ ፈጠራ
አዲሱ ፈጠራ ወላጆች ልጆቻቸው ከመወለዳቸው በፊት በሚፈልጉት ጾታ፣ ቁመት እና የማሰላሰል አቅም እንዲወስኑ የሚያደርግ ነው ተብሏል
ወላጆች የአዲሱ ፈጠራ አገልግሎትን ለማግኘት 50 ሺህ ዶላር መክፈል እንዳለባቸው ተገልጿል
ልጆች ከፍተኛ የማሰላሰል አቅም ይዘው እንዲወለዱ የሚያደርገው አዲስ ፈጠራ
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው አዲስ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ለማሰብ የሚከብዱ ፈጠራዎችን ለአገልግሎት አብቅቻለሁ ብሏል፡፡
ሄሊዮስፔክት ጄኖሚክስ የተሰኘው ይህ አዲስ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ልጆች ከመወለዳቸው በፊት ከፍተኛ የማሰላሰል አቅም ወይም አይኪው እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡
ኩባንያው ላለፉት ዓመታት በተለይም በሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ ወይም በህክምና እገዛ በሚወለዱ ህጻናት ላይ በርካታ ሙከራዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ዘ ጋርዲያን አስነብቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ቴክኖሎጂው ወላጆች ልጃቸው በሚፈልጉት ጾታ፣ ቁመት፣ የማሰላሰል አቅም መጠን እና ሌሎችም እንዲወለድ የሚያደርግ ነው፡፡
ልጆቼ ትኩረት አልሰጡኝም ያሉ ወላጅ ንብረታቸውን ለውሻቸው አወረሱ
ወላጆች ይህን አገልግሎት ለማግኘት እስከ 50 ሺህ ዶላር መክፈል የሚጠበቅባቸው ሲሆን አገልግሎቱን እያገኙ ያሉ ወላጆች እንዳሉም ተገልጿል፡፡
እስካሁን ለ12 ልጆችን በተፈጥሮ መንገድ መውለድ ላልቻሉ ነገር ግን በህክምና እገዛ ለወለዱ ወላጆች አገልግሎቱ ተሰጥቷቸዋል የተባለ ሲሆን ህጻናቱ በዚህ ቴክኖሎጂ የማሰላሰል አቅማቸው በተፈጥሯቸው ሊያገኙ ከሚችሉት ስድስት እጥፍ የተሻለ ነውም ተብሏል፡፡
ቴክኖሎጂው የማሰላሰል አቅም ወይም አይኪውን ከመጨመር በተጨማሪ ሊከሰቱ የሚችሉ እንደ የአዕምሮ ህመም፣ ከመጠን በላይ ውፍረት እና ሌሎች ስጋቶች ህጻናቱን እንዳያጠቁ የሚያደርግ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ይህ ቴክኖሎጂ ለአገልግሎት መብቃቱን ተከትሎ አድናቆት እና ትችቶችን ያስተናገደ ሲሆን ቴክኖሎጂው የማህበረሰብ ልዩነት እንዲፈጠር የሚያደርግ እና ተፈጥሮን የሚጋፋ ነው የሚል ትችት ቀርቦበታል፡፡
ቴክኖሎጂውን ያበቃው ኩባንያ በበኩሉ አገልግሎቱ ገና በጅምር ላይ መሆኑን እና በቀጣይ ለሁሉም ማህበረሰብ እንዲቀርብ ሊደረግ እንደሚችል አስታውቋል፡፡
ሁሉም ወላጅ ከበሽታ ነጻ የሆነ ልጅ እንዲኖረው ይፈልጋል አዲሱ ቴክኖሎጂም ይህን መነሻ በማድረግ መልማቱንም ኩባንያው አስታውቋል፡፡