ፖሊስ በአዲስ አበባ ወላጅ አባቱን በቤንዚን አቃጥሎ የገደለን ተጠርጣሪ መያዙን ገለጸ
ተጠርጣሪው ድርጊቱን የፈጸመው አባቴ እና ወንድሜ ለኔ ቦታ የላቸውም በሚል ነው ተብሏል
ግለሰቡ ከዚህ በፊትም በሌላ ወንጀል ተጠርጥሮ ከታሰረበት ቦታ በዋስትና እንደወጣ ተገልጿል
ፖሊስ በአዲስ አበባ ወላጅ አባቱን በቤንዚን አቃጥሎ የገደለን ተጠጣሪ መያዙን ገለጸ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ቤተሰቦቼ ለእኔ ምንም ቦታ የላቸውም በሚል ምክንያት ወላጅ አባቱንና ታላቅ ወንድሙን ቤንዚል በመርጨት በቁም ያቃጠላቸው ተከሳሽ በቁጥጥር ማዋሉን ገልጿል።
ተከሳሹ የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመው በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ክብረ ደመና ሙሉ ወንጌል አካባቢ ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ/ም ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ነው ተብሏል።
ተከሳሹ ከዚህ ቀደም በሌላ ወንጀል ተከሶ ታስሮ የነበረና በፍርድ ቤት ዋስትና የተለቀቀ እንደነበር የገለጸው ፖሊስ ከእናቴ በስተቀር ለእኔ የሚያስብልኝ የለም በሚል ምክንያት ወንጀሉን ለመፈጸም እንደተነሳሳም ተገልጿል።
ከሳምንት በፊትም በአንድ ሺህ ስድስት መቶ ብር ቤንዚል በመግዛት አባቱና ታላቅ ወንድሙ የግል ጉዳያቸውን ፈፅመው በመምጣት ቤት ውስጥ ቁጭ ባሉበት ወቅት ወንጀሉን ፈጽሟል ተብሏል።
ይህ ተጠርጣሪም እናትዬውን ውሃ አምጭልኝ ብሎ ከቤት መውጣታቸውን ጠብቆ ቤንዚሉን አርከፍክፎባቸው ክብሪት በመለኮስ ማምለጥ እንዳይችሉ በሩን ቆልፎ ለማምለጥ ሞክሮ እንደነበርም ፖሊስ አስታውቋል።
ተጎጂዎችን ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር ወደ ህክምና ቢወስዱም አባትዬው ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ታላቅ ወንድሙ በህክምና ላይ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።
በተያያዘ ዜና ፖሊስ በአራዳ ክፍለ ከተማ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ በሞባይል ጥገና ስራ የተሰማራ ግለሰብ የተሰረቁ ስልኮችን ከሌቦች ይገዛ እንደነበር ደርሼበያለሁ ብሏል።
ከዚህ ተጠርጣሪ ላይም 33 የተሰረቁ የእጅ ስልኮችን በኢግዚቢትነት መያዙንም ፖሊስ ገልጿል።