ፖለቲካ
ሱዳን የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዤ መለስኩ የምትለው የተሳሳተ ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
“ሱዳኖች መሬታችንን ወረው ያዙ እንጂ እስካሁን የገጠምነው ጦርነት የለም”- አምባሳደር ዲና
በኢትዮጵያ በመንግሥት በኩል ዝም የተባለ ነገር የለም
ሱዳን የኢትዮጵያ ወታደሮችን “ይዤ መለስኩ” የምትለው ፍጹም የተሳሳተ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፤ ሱዳን 61 የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዣለሁ ማለቷ የተሳሳተ ነው ብለዋል።
“ሱዳን የያዘችው የኢትዮጵያ ወታደር የለም” ያሉት አምባሳደር ዲና፤ “በሱዳን ተይዘው የነበሩት 59አረሶ አደሮች እና 2 ሚሊሻዎች ናቸው” ሲሉም አስታውቀዋል።
“በሱዳን ተይዘው የነበሩ ሰዎች አሁን እዚህ ናቸው የማያሰጋ ነገር የለውም” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ይመለሱ በሚል የሚሰራ ነገርም የለም ብለዋል።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በመግለጫቸው አክለውም “ሱዳኖች መሬታችንን ወርረው ያዙ እንጂ እስካሁን የገጠምነው ጦርነት የለም” ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አሁንም ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ጉዳይ ቀደም ሲል በተቋቋመው የድንበር የጋራ ኮሚቴ ይፈታ የሚል አቋም እንዳላትም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ የሱዳን አካሄድ ልክ እንዳልሆነ እያስተጋባች መሆኑን በማንሳት፤ “በመንግሥት በኩል ዝም የተባለ ነገር የለም” ሲሉም ተናገረዋል።