“የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ውዝግብ በሁለትዮሽ ድርድር ብቻ ነው መፈታት ያለበት” ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ሱዳን ያለምንም ጥናት “በቀጥታ ድንበር እንዲካለል” እንደምትፈልግ የኢትዮጵያ ውጭ ጉ/ሚ አማካሪ ገልጸዋል
ኢትዮጵያ “እውነታውን የሚያጠና የጋራ ኮሚሽን ወደ ድንበር ተልኮ የጥናት ውጤት እንዲያመጣ” ትፈልጋለች
ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ በነበረችበት ወቅት በሱዳን ወረራ እንደተፈጸመባት የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ መግለጹ የሚታወቅ ነው፡፡
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ ያደረጉት ፣ በድንበር ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የቴክኒክ አማካሪ እና የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ የድንበር ኮሚሽን አባል ውሂብ ሙሉነህ “ሱዳኖች እምነትም አጉድለዋል” ይላሉ፡፡
በጋብቻ ፣ በንግድ እና በባህል በተሳሰሩት በድንበር አካባቢ ባሉ የሁለቱ ህዝቦች መካከል የጠላትነት ስሜት እንደሌለ የሚያነሱት አቶ ውሂብ ፣ ችግሮች የሚፈጠሩት የመንግስት ለውጥ በሚኖርበት ጊዜ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ አክለውም “ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ሕግ በምታስከብርበት ወቅት የሱዳን መንግስት ድንበሩን ለመዝጋት ተስማምቶ ነበር” ያሉ ሲሆን “ይህ በመልካም መተማመን ላይ የተመሰረተ ነበር” ብለዋል፡፡ ነገር ግን ሱዳን አጋጣሚውን ተጠቅማ ወረራ መፈጸሟን ነው ያነሱት፡፡
የሁለቱ ሀገራት የድንበር ውዝግብ ከ100 ዓመታት በላይ የቆየ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ውሂብ ፣ በተባበሩት መንግስታት የተመዘገበው የ1972ቱ የሁለቱ ሀገራት የድንበር ስምምነት ችግሩ እንዴት መፈታት እንዳለበት ይደነግጋል ብለዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ የድንበር ውዝግቡን ለመፍታት የተለያዩ ዘዴዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ስምምነቱ የሚያዝ ሲሆን እነዚህም የጋራ የድንበር ኮሚሽን ፣ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ፣ የጋራ ልዩ ኮሚቴ መፍትሔዎችን ያካትታሉ፡፡ ለውዝግቡ የመጨረሻ ውጤት እስኪገኝ ነባራዊው ሁኔታ እንዲቀጥል የሚደነግገው የ1972ቱ ስምምነት በሁለቱም ሀገራት ሊከበር ቢገባውም ፣ የኃይል ወረራ በመፈጸም ሱዳን ስምምነቱን እንደጣሰች ነው ያብራሩት፡፡
የጋራ ልዩ ኮሚቴ ለድንበር ውዝግቡ ፍቱን መፍትሔ እንዲያመጣ የተመሰረተ ዋነኛው ኮሚቴ መሆኑን በመጥቀስ ፣ ኢትዮጵያ ይህ ልዩ ኮሚቴ የመጨረሻ የመፍትሔ ሀሳብ ይዞ እንዲመጣ ፍላጎቷ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አቶ ውሂብ “የድንበሩ ጉዳይ ከቁጥጥር ውጭ የሚሆን አልነበረም” ካሉ በኋላ ታህሳስ ወር ላይ በካርቱም በነበረው የፖለቲከኞች የጋራ ከፍተኛ ኮሚሽን ፣ በንግግር ለመፍታት ስምምነት ተደርሶ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡
“እውነቱን የሚያጠና የጋራ ኮሚሽን ወደ ድንበር እንላክ እና በመሬት ላይ ያለውን አጥንቶ ውጤቱን ያምጣ” የሚል ሀሳብ በኢትዮጵያ በኩል ተነስቶ ነበር የሚሉት አቶ ውሂብ በሱዳን ወገን ደግሞ “ቀጥታ ሔደን ድንበር እናካልል” የሚል ሀሳብ ነው የተነሳው ብለዋል፡፡ ጦርነት እያለ ቀጥታ የማካለል ስራ መስራት እንደማይቻል በመግለጽ ሰላም ሳይኖር የሰርቬይ ፣ የካርታ እና የጂኦግራፊ ባለሙያዎች ሄደው መስራት እንደማይችሉም የኢትዮጵያን አቋም አቶ ውሂብ አንጸባርቀዋል፡፡
ለሱዳን እና ለኢትዮጵያ መፍትሔው “አንዳችን ሌላኛችንን መተቸት አይደለም” የሚሉት ባለሙያው “አሁንም ትክክለኛው መፍትሔ ሦስተኛ ወገን የሌለበት የሁለትዮሽ ድርድር ነው” ሲሉ ሁለቱ ሀገራት ችግሩን ብቻቸውን መፍታት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ከ1972ቱ አስገዳጅ ስምምነት በኋላ የተመሰረቱት የጋራ የድንበር ኮሚሽን ፣ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ እና የጋራ ልዩ ኮሚቴዎችን በመጠቀም የመፍትሔ አቅጣጫዎችን እንደገና መጀመር አስፈላጊ እንደሆነም አንስተዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት አሁን ከገቡበት ማጥ የሚያወጣቸው ይህ አማራጭ እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ወደ ድርድር ለመመለስ ሱዳን ከጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በወረራ ከያዘችው ግዛት ለቃ መውጣት እንዳለባት ኢትዮጵያ ቅድመ ሁኔታ ብታስቀምጥም ፣ ሱዳን ቅድመ ሁኔታውን እንደማትቀበል ገልጻለች፡፡