ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ጉዳይ ግጭት ውስጥ ቢገቡም የድንበር ላይ ንግዱ አልተቋረጠም-የአካባቢው ባለስልጣን
የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳን የአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ለማወቅ እየተንቀሳቀሰች ነው ሲል ከሷል
የድንበሩ ግጭቱ መተማና ጋላባት በተባሉ የድንበር ከተሞች መካከል በሚደረገው የንግድ ልውውጥ ላይ ተጽእኖ አላሳደረም ብለዋል ከንቲባው
ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ግጭት ምክንያት ከባለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ግንኙነታቸው ቢሻክርም፣ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ የነበረው የንግድ ልውውጥ እስካሁን አለመቋረጡን የአካባቢው ባለስልጣን ገልጸዋል፡፡
የመተማ ዮኃንስ ከተማ ከንቲባ ሀብቴ አዲሱ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ዋነኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር የሚያገናኘው በመተማ በኩል ያለው ትልቁ መስመር አሁን የተለመደ የትራንስፖርት አገልግሎት እያስተናገደ ነው፡፡
ከንቲባው በኢትዮጵያዋ የድንበር ከተማ (መተማ)ና በሱዳኗ የድንበር ከተማ (ጋላባት) መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ መቀጠሉንና፤ በድንበሩ ግጭት ምክንያት አለመቋረጡን ተናግረዋል፡፡ በድንበር አካባቢ ያለው የህዝበብ ለህዝብ ግንኙነት መልካም መሆኑን የገለጹት ከንቲባ ሀብቴ እስከ 12 ሰአት ድረስ ሱዳናውያ ወደ ኢትዮጵያ መግባት ይችላሉ፤ ኢትዮጵያውያንም እስከ 12 ሰአት ድረስ የሱዳንን ድንበር አቋርጠው መግባት ይችላሉ ብለዋል፡፡
ከንቲባው የሁለቱ ከተማ አመራራሮች እንደሚገኙና እንደሚመካከሩ ገልጸዋል፡፡
ነገርግን እንደ ከንቲባ ሀብቴ ገለጻ ከመተማ ከተማ ከ10-15 ኪ.ሜ ባለው ርቀት ላይ ችግር መሆኑና በመጋቢት ወር ብቻ 5 ኢትዮጵያውን አርሶ አደሮች መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡
ግጭቱ አሁንም አለመቆሙን የገለጹት ከንቲባው የሱዳን ወታደሮች በኢትዮጵውያን የሚታሩስትን ቦታዎች መያዛቸውን፤ የደረሰ ሰብል መውሰዳቸውንና በመተማ ዙሪያ ወረዳ ደለሎ የተባለ የእርሻ መሬት መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡
ከንቲባው እንዳሉት የእርሻ ወቅት (ሰኔና ግንቦት) ሳይደረስ መንግስት ደርሶ ካላስለቀቀ፤ ግጭት ሊከሰት እደንሚችል ገልጸዋል፤ የአካባቢው ህዝብም መንግስት ቀደም ብሎ ደረሶ መፍትሄ እንዲሰጥ እየጠየቁ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያና ሱዳን ግጭት
የኢትዮጵያ መንግስት መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል ለህግ ማስከበር ዘመቻ መንቀሳቀሱን ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ መግባቱን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ከሳለች፡፡
የሱዳን ጦር ከፈረንጆቹ ኅዳር 6 ጀምሮ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት፤በቦታው በነበሩ የአርሶ አደሮች ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን መንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ጉዳይ እልባት ለመስጠት፤ ሱዳን ወደ ቀደመ ቦታዋ መመለስን እንደቅድመ ሁነታ አስቀምጧል፡፡
በዛሬው እለት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትዊትር ገጹ እንደጻፈው “ሱዳን የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የበይነ መንግስታት ድርጅት ሊቀመንበር ሆና” ሳለች በኢትዮጵያ ላይ ወረራ መፈጸሟ “የሚያጸጽት” መሆኑን ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ ሰዱን “ኢትዮጵያን በመውረር፣ ንጹሃንን በማፈናቀልና ተጨማሪ መሬቶችን ለመውረር የጦርነት ከበሮ በመምታት የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነትን አደጋ ላይ ጥላለች” ሲል ገልጿል፡፡
ነገርግን ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ አለመግባቷንና የሱዳን ጦር የያዘው ቦታ የሯሳ ግዛት አካል ነው በማለት ክሱን አትቀበልም፡፡