137 ኢትዮጵያውያን ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከጠ/ ሚ/ር ዐቢይ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡
ችግር ውስጥ የነበሩ 137 ኢትዮጵያውያን ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከጠ/ ሚ/ር ዐቢይ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በ3 ቀናት የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸው ከኢትዮጵያውያን ጋር ከነበራቸው ቆይታ በተጨማሪ ከአቡዳቢ ልዑል እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጦር ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ተወያይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልዑሉ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ውይይት፣ የሀገራቱ ግነኙነት አሁን የደረሰበትን ደረጃ በማድነቅ በቀጣይ የበለጠ እንዲጠናከር የተለየ ትኩረት እንደሚሰጡ አንስተዋል፡፡
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በህገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውንን ህጋዊ ለማድረግ ሁለቱ አካላት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በሀገሪቱ በልዩ ልዩ ምክንያቶች እስር ቤትና በመጠለያ የነበሩ እንዲሁም መደበኛ ባልሆነ ስደት ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የገቡ ዜጎች ምህረት የተደረገላቸው ሲሆን፣ በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ለመኖር የሚፈልጉ ህጋዊ መኖሪያ ፈቃድ ተሰጥቷቸው እንዲኖሩ ተፈቅዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከየካቲት 5 እስከ 7 ቀን 2012 ዓ.ም የቆየውን ጉብኝታቸውን አጠናቀው ሲመለሱ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች በችግር ውስጥ የነበሩ 137 ኢትዮጵያውያንን ይዘው ትናንት እኩለ ሌሊት ገደማ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጉብኝታቸው ወደተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በህገ ወጥ መንገድ ገብተው ችግር የደረሰባቸው ዜጎችን በአቡዳቢ አግኝተው ባወያዩበት ወቅት ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉትን ይዘዋቸው እንደሚመለሱ ቃል በገቡት መሠረት ነው 137 ዜጎችን ይዘው የተመለሱት፡፡ የተመለሱት ኢትዮጵያውያን የጉዞ ሰነድ በማጣት ከሀገር እንዳይወጡ ለዓመታት ተከልክለው የቆዩ ነበሩ።
ከሁለትዮሽ ጉዳዮች በተጨማሪ በአካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይም ሁለቱ ሀገራት በትብብር ስለመስራት ውይይት አድርገዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ልጆች የሚማሩበት ትምህርት ቤት ለመክፈት ከስምምነት ተደርሷል።
በጉዞው በተደረገ የዲፕሎማሲ ስራ በአቡዳቢ ለኢትጵዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ህንጻ ማሰሪያ ቦታ የተፈቀደ ሲሆን፣ በዱባይ እና ሻርጃ ግዛቶች አማካይ ስፍራ ለፕሮቴስታንት አማኞችም የጸሎት ቦታ በኤክስፖ 2020 ከሚሰራ ህንፃ እንዲሰጥ መወሰኑን በሀገሪቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ተናግረዋል።
ምንጭ፡- ኤፍቢሲ