በየመን በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ ደረሰ የተባለውን ጉዳት በተመለከተ እየተከታተለ እንደሆነ መንግስት አስታወቀ
ከ45 ሰዎች መሞታቸው እና ከ250 የሚልቁ ሰዎች መጎዳታቸውም ተሰምቷል
አደጋው በሰንዓ እስር ቤት ላይ የደረሰ ነው የተባለ ሲሆን ኢትዮጵያውያኑን ጨምሮ በርካቶች መጎዳታቸው ተነግሯል
የካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም በየመን ዋና ከተማ ሰንዓ ማቆያ እስር ቤት ላይ በተከሰተ የእሳት አደጋ በእስር ቤቱ ውስጥ በነበሩ እስረኞች ላይ የሞትና የቁስለት አደጋ እንደደረሰ በሙስካት (ኦማን) የሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በላከው ደብዳቤ አሳውቋል።
የአደጋው መንስኤ የእሳት ቃጠሎ ነው ያለው ኤምባሲው የቃጠሎው መነሻ ከየመን ተፋላሚዎች ጋር የተገናኘ ስለመሆኑና አለመሆኑ፣ ምንያህል ሰዎች እንደተጎዱ እና ከተጎጂዎቹ መካከል ምን ያህሉ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ለማወቅ እያጣራ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ጉዳዩን በትኩረት በመከታተል መንግስት የተረጋገጠ መረጃ ይፋ የሚያደርግ እንደሚሆንም ነው ኤምባሲው በመግለጫው የጠቆመው።
ኤምባሲው በአደጋው ለጠፋው የዜጎች ሕይወትና ለደረሰው የአካል ጉዳት የተሰማውን ከፍተኛ ሃዘንም ገልጿል፡፡
ይሁንና ኤምባሲው ህገወጥ የዜጎች ጉዞ ጉዳቱን ያከፋእና የተሟላ መረጃ ለማግኘት አዳጋች እንዳደረገው አልሸሸገም፡፡
በመሆኑም ዜጎች ወደ ውጭ ሃገራት በነጻና ሕጋዊ መንገድ የመንቀሳቀስ መብታቸው በሕገ መንግስቱ የተደነገገ ቢሆንም በሕጋዊ መንገድ ብቻ ከሃገር ቢወጡ መሰል አደጋዎችን ለመከላከል እና መብታቸውን ለማስከበር እንደሚረዳ ጠቁሟል።
ከዚህ አንጻር መንግስት ከተለያዩ ሃገራት ጋር በዋናነትም ከመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ጋር የተለያዩ የአሠሪና ሠራተኛ ውሎችን እየተፈራረመም እንደሆነም ነው የገለጸው።