የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተኩስ አቁም ቢያውጁም ትናንት በካርቱም ዳርቻ ተዋግተዋል
የሱዳን ጦር በዛሬው እለት የሚያበቃውን የተኩስ አቁም ስምምነት "ለማራዘም ፍቃደኛ ነኝ" አለ።
ለ12 ቀናት በዘለቀው የሱዳን ግጭት ለሁለተኛ ጊዜ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መጣሱ እየተነገረ ነው።
ተዋጊ ኃይሎቹ ያወጁት የሦስት ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ዛሬ ሀሙስ ምሽት ላይ ያበቃል።
ነገር ግን የሱዳን መከላከያ ሰራዊት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራዘም ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል።
የጦር ኃይሉ መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ስምምንቱን ለተጨማሪ 72 ሰዓታት ለማራዘም እና ለንግግር ወደ ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ የጦር መልዕክተኛ ለመላክ የመጀመሪያውን ፍቃድ መስጠታቸውን አስታውቀዋል።
የሱዳን ጦር የደቡብ ሱዳን፣ የኬንያ እና የጅቡቲ ፕሬዝዳንቶች የስምምነት ማራዘሚያ እንዲሁም በሁለቱ ኃይሎች መካከል የሚደረግን ውይይት የሚያካትት ምክረ-ሀሳብ ማዘጋጀታቸውን ገልጿል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሀማት ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም በጋራ ለመስራት መወያየታቸውም ተነግሯል።
የረቡዕው ጦርነት በአብዛኛው ከካርቱም አጠገብ በምትገኘው በኦምዱርማን ከተማ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።