የሱዳን ጦርነት ለጎረቤት ሀገራት ያለው ዳፋ ምንድን ነው?
የጦርነቱ መራዘም በሀገራቱ ላይ የስደተኞች ጎርፍ፣ የነዳጅና ሌሎች የወጪ ንግድ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎልን እንደሚያስከትል ይጠበቃል
ሱዳን ድንበር ከምትጋራቸው ሰባት ሀገራት አምስቱ ባለፉት አመታት በጦርነት ውስጥ ቆይተዋል
ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ሱዳን በ2019 ኦማር ሀሰን አልበሽር በመፈንቅለ መንግስት ከተነሱ በኋላም ሆነ በፊት አደባባዮቿ በተቃዋሚዎች እንደተሞሉ ነው።
ካርቱም ሺዎችን የሚቀጥፍና የሚያፈናቅል ጦርነት ብርቋ ባይሆንም ከ12 ቀናት በፊት የተቀሰቀሰው ግጭት ግን እጅግ ፈታኝ እንደሆነባት እየታየ ነው።
ሀገራት ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማስወጣት መሯሯጥን ሲይዙ ጎረቤቶቿ ደግሞ በገፍ የሚገቡ የሱዳን ስድተኞችን በመቀበል ተጠምደዋል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ወደ ቻድ እና ደቡብ ሱዳን የገቡ ሲሆን፥ በቀጣይ ቀናትም አሃዙ ከፍ እንደሚል ነው የሚጠበቀው።
ጦርነቱ የስደተኞች ጎርፍን ከማስከተሉ ባሻገር ከካርቱም ጋር ጥብቅ የንግድ ግንኙነት ያላቸውን ጎረቤቶቿን ክፉኛ እንደሚጎዳ ተነግሯል።
የካርቱም ወቅታዊ ሁኔታ ለጎረቤቶቿ ዳፋው ምንድን ነው?
ግብጽ
ግብጽ እና ሱዳን በአባይ ውሃ የተጋመደ የታሪክ፣ ባህል፣ ንግድ እና ፖለቲካዊ ትስስር አላቸው። በግብጽ ከ4 ሚሊየን በላይ ሱዳናውያን መኖራቸውም የግንኙነቱን ስፋት ያሳያል። ይሁን እንጂ ለረጅም ጊዜ ግብጽ በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ እጇ ረጅም እየረዘመ መሄዱ ሱዳናውያን ጭምር በተደጋጋሚ ሲቃወሙት ይደመጣል።
ለሱዳን ጦር መሪው ጀነራል አልቡርሃን ድጋፍ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ በሱዳን የተቀሰቀሰውን ጦርነት በትኩረት እንዲከታተሉ የሚያደርጋቸው ጉልህ ጉዳይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ እንደሆነ ሬውተርስ አስነብቧል። የጦርነቱ እየተራዘመ መሄድ አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ ግድቡን እንድትሞላ ያደርጋታል የሚል ስጋት እንዳላቸውም በማከል።
ኢትዮጵያ
በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከ50 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን ተሰደዋል፤ ሱዳንም በጦርነቱ ወቅት የአልፋሽጋ አካባቢን መያዟ ይታወሳል። ይህ የድንበር ውዝግብ እስካሁን አልተፈታም። በአሁኑ ወቅት እየተፋለሙ የሚገኙ የሱዳን ጀነራሎችን ለማደራደር ፍላጎቷን የገለጸችው ኢትዮጵያ፥ የድንበር ውዝግቡን በድርድር መፍታት እንደምትመርጥ አስታውቃለች። የጦርነቱ እየተራዘመ መሄድና የሀገራት አሰላለፍ ግን ነገሮችን ሊለዋውጥ እንደሚችል ተንታኞች ያነሳሉ።
ሊቢያ
ሊቢያ ከ2011 ጀምሮ ጦርነት ውስጥ ስትገባ የሱዳን ቅጥረኛ ወታደሮች እና ሚሊሻዎች በሁለቱም ተፈላሚ ወገኖች ጎራ ተሰልፈው ተዋግተዋል። የሱዳን ተዋጊዎች ወደ ሀገራቸው ሲመለሱም በዳርፉር ለተነሳው ደም አፋሳሽ ጦርነት ድርሻ እንደነበራቸው ይነገራል። ሱዳን በሊቢያ በኩል ስደተኞችን ወደ አውሮፓ ለማሻገር መተላለፊያ መሆኗ ይታወቃል። አሁን ላይ ካርቱም የገጠማት ፈተና ወደ ትሪፖሊ በመግባት በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚሳተፉ ሱዳናውያን ደላሎችን እንዳያበራክት ስጋት ፈጥሯል።
ቻድ
ከሱዳን ጋር ከ1 ሺህ 400 ኪሎሜትር በላይ ድንበር የምትጋራው ቻድ፥ ከ400 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ነው። ከ12 ቀናት በፊት የተቀሰቀሰው ጦርነትን ሽሽትም 20 ሺህ የሚጠጉ ሱዳናውያን የቻድን ድንበር አልፈው ገብተዋል።
በዳርፉር ጦርነት ወቅት ጃንጃዊድ የተሰኘው የሱዳን ሚሊሻ ቡድን (በኋላ አርኤስኤፍን የተቀላቀለ) የቻድን ድንበር እየጣሰ በመግባት ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል። በትናንትናው እለትም ከ320 በላይ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል አባላት ወደ ቻድ ዘልቀው ለመግባት ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር አውሎ ትጥቅ እንዳስፈታ የቻድ መንግስት ገልጿል። የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ከቻድ አማጺያን ጋር ጥምረት ሊመሰርት ይችላል የሚለውም ኢንጃሚናን ከስደተኞች መበራከት ባለፈ የደህንነት ስጋት እንደተደቀነባት ያሳያል።
ደቡብ ሱዳን
በፈረንጆቹ 2011 ከሱዳን ተነጥላ ሉአላዊ ሀገር የሆነችው ደቡብ ሱዳን በቀን 170 ሺህ በርሚል ነዳጇን ወደ ፖርት ሱዳን የምትልከው ካርቱምን አቋርጦ በሚያልፍ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ነው። ሁለቱም የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች የነዳጅ ማስተላለፊያው ላይ ጥቃት እንደማይሰነዝሩ ቢገልጹም ጁባ ከፍተኛ ስጋት አላት።
በሱዳን ከ800 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች አሉ። የጦርነቱ መባባስም ደቡብ ሱዳናውያኑን ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚሉ ተንታኞች፥ ይህም ለጁባ መንግስት ተጨማሪ ጫናን ሊፈጥር እንደሚችል ያነሳሉ።
የሱዳን ጦርነት ሁለንተናዊ ተጽዕኖ በጦርነቱ እጃቸውን የሚያስገቡ የውጭ ሃይላት እየሰፋ ሲሄድ ይበልጥ አስቸጋሪ እና በአጭሩ የማይቆም ይሆናል።