በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች ተፈጥረው በነበሩ “ግጭቶች” የሱዳን እና ግብፅ ድጋፍ እንደነበረበት ምክር ቤቱ ገለጸ
ከ68 ሺ በላይ የጉሙዝ ማኅበረሰብ አባላት ሸሽተው ጫካ ገብተው ነበርም ተብሏል
ምክር ቤቱ በሱዳን ድንበር ላይ ታጣቂዎችን የማሰልጠን እና ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ንግዶች ሲከናወኑ እንደነበር አስታውቋል
በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች የሱዳን እና ግብፅ ድጋፍ እንደነበረበት ምክር ቤቱ ገለጸ፡፡
ግጭቶቹን በመገምገም የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያቀርብ በምክር ቤቱ የተቋቋመው ኮሚቴ ከትግራይ ክልል ውጭ ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች የሱዳን እና የግብጽ ድጋፍ እንደነበረበት ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ኮሚቴው የደረሰበትን የግምገማ ሃሳብ በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል አል ዐይን አማርኛ ከምክር ቤቱ ይፋዊ ማህራዊ ገጽ እንዳገኘው መረጃ ከሆነ፡፡
መግለጫውን የሰጡት የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አብዱላሂ ሀሙ በሱዳን ድንበር ላይ ታጣቂዎችን የማሰልጠን እና ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ንግዶች ሲከናወኑ እንደነበር ከሕብረተሰቡ እና ከመተከል ኮማንድ ፖስት መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡
የተፈጠሩት ግጭቶች ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ ረዘም ያለ ዝግጅት ሲደረጉባቸው የነበሩ ናቸው ያሉት ሰብሳቢው በኢንቨስትመንት ስም በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ አካላት “ክልሉ ሊፈርስ ነው ልትወረሩ ነው፣ ታጠቁ፣ ተዘጋጁ” እያሉ ይቀሰቅሱ እንደነበር አብራርተዋል፡፡
በዚህም ከ68 ሺ በላይ የጉሙዝ ማኅበረሰብ አባላት ሸሽተው ጫካ መግባታቸውን ነው የገለጹት፡፡ ሆኖም አሁን አብዛኞች ተመልሰዋል ብለዋል፡፡ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ እጃቸውን የሰጡ 3 ሺ ገደማ ታጣቂዎች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ መደረጉንም ነው አቶ አብዱላሂ የገለጹት፡፡
የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ከ10 ሺህ የሚበልጡ ሚሊሻዎችን በመመልመልና በማሰልጠን የዝግጅት ስራ እየተሰራ ነውም ብለዋል ሰብሳቢው፡፡
በግጭቱ እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ የክልሉና አንዳንድ የፌዴራል የየደረጃው አመራሮች ከኃላፊነት ተነስተው በህግ የተጠያቂነት ሂደት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ከኮማንድ ፖስቱ ተረድተናል ብሏል ግጭቱ ሌላ ፍላጎት ያላቸው አካላት እንጂ የህዝብ ለህዝብ አይደለም ያለው ኮሚቴው፡፡
በግጭቱ 125 ሺ ገደማ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቀለዋል፤ ንብረታቸውም ወድሞባቸዋል፡፡ በተጠለሉባቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ሆኖም የተፈናቃዮቹ ቁጥር ከፍ ከማለቱ የተነሳ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በቂ ድጋፍ የማይደርስበት ሁኔታ አለ እንደ ሰብሳቢው ገለጻ፡፡
ይህን ለመፍታት በቅንጅት መሰራት አለበት ያሉት አቶ አብዱላሂ መንግስት የተፈናቀሉትን ዜጎች ወደ ቦታቸው የመመለስ፣ የተጎዳ ስነ-ልቦናቸውን የመገንባት እና አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ ስራ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡