የግድቡ ድርድርም በቅርቡ እንደሚቀጥል የሱዳን ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል
የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦማር ቀመረዲን እስማኤል፣ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የገባችበትን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት በሁለቱ ሀገራት መካከል በቅርቡ ስምምነት እንደሚደረስ ገልጸዋል፡፡
ቀመረዲን ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በአጎራባች ሀገራቱ መካከል የድንበር ውዝግቦች የተለመዱ እንደሆኑ እና በድርድር እንደሚፈቱ አመልክተዋል ፡፡
ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች ጋር ባላት የድንበር ውዝግብ ሁሉንም ዓለም አቀፋዊ ህጎች እና ደንቦች እንደምታከብር ፣ እንዲሁም በሌሎች ሀገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባም ነው ያነሱት፡፡
የህዳሴ ግድብን ድርድር በማስመልከት ባደረጉት ንግግር “በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአዲስ መልክ ወደ ድርድር ለመመለስ እየተዘጋጀን ነው ፤ ከውይይት ውጭ ምንም አማራጭ የለም” ብለዋል፡፡ “የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች በግድቡ ድርድር ላይ የላቀ ሚና እንደሚኖራቸው እንጠብቃለን” ሲሉም አክለዋል፡፡
“ሱዳን እና ግብፅ በህዳሴ ግድብ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ አስገዳጅ የሆነ ስምምነት እንዲደረስ ጥሪ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል” ያሉት ተጠባባቂ ሚኒስትሩ ሀገራቸው ከቀደመው ስርዓት ከባድ ውርስ እንደወረሰች በመግለጽ ሱዳንን እንደገና መገንባት ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡