ሱዳን በድንበር አካባቢ የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንድታቆም ኢትዮጵያ አሳስባለች
ከትናንት ጠዋት ጀምሮ እስከ ዛሬ በሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ላይ በሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል በካርቱም የተደረገው የጋራ ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ ያለስምምነት መጠናቀቁን የሱዳን የሽግግር መንግስት ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የሱዳን ወገን በካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አምባሳደር ኦማር በሽር ማኒስ የተመራ ሲሆን የኢትዮጵያ ልዑክ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ነው፡፡
ምንጮቹ እንዳመለከቱት በአወዛጋቢው የድንበር ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር የጋራ ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴው ውይይት በሌላ ጊዜ እንዲቀጥል ተለዋጭ ቀጠሮ ተይዟል፡፡
አሁን በድንበር ላይ ስላለው ሁኔታ ውይይት እንዲደረግ ትናንት ከኢትዮጵያ በኩል የቀረበውን ጥያቄ ሱዳን መቀበል እንዳልፈለገች የሀገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
ሱዳን አሁን ከድንበር ማካለል ጉዳይ ውጭ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ ባለፉት ቀናት በተፈጠረው ጉዳይ ላይ መወያየት እንደማትፈልግ ገልጻለች ነው የተባለው፡፡
የሱዳን መንግስት “ላለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ የተያዘብኝን መሬት በወታደራዊ ኃይል አስመልሼ በድንበር አካባቢ ሉዓላዊነቴን አስከብርያለሁ” በማለት መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
በትናንትናው ዕለት የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ካርቱም ላይ ባደረጉት ንግግር ከጥቅምት 30 ጀምሮ የሱዳን ጦር በኢትዮጵያ ላይ ፣ በከባድ መሳሪያዎች እና በወታደራዊ ተሸከርካሪዎች በመታገዝ ፣ ጥቃት ሲፈጽም መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጦር በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከጀመረ ከ6 ቀናት በኋላ የተጀመረው የሱዳን ጦር ጥቃት ፣ የቀደሙ ስምምነቶችን የሚጥስ መሆኑን ኢትዮጵያ አስታውቃለች፡፡ በመሆኑም ሱዳን ከዚህ ድርጊቷ እንድትቆጠብ ነው የኢትዮጵያ ልዑክ ያሳሰበው፡፡ ይሁን እንጂ ሱዳን በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ አስመልሻለሁ ባለችው አካባቢ ከፍተኛ ጦር አስፍራለች፡፡
ሱዳን በድንበር አካባቢ የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንድታቆም እና ነገሮች ወደ ቀደመ ቦታቸው እንዲመለሱ ኢትዮጵያ ማሳሰቧን ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡ በአርሶአደሮች እና ባለሃብቶች ንብረት ላይ የደረሰው ከፍተኛ ጉዳት እና የዜጎች መፈናቀል ትኩረት እንደሚያሻውና በአስቸኳይ መታረም እንዳለበትም ነው ያሳሰበችው፡፡
“ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በድንበር ላይ ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ ለሚፈጠር ማንኛውም ጉዳይ ዝግጁ ናት” ሲሉ የሱዳን መንግሥት ቃል አቀባይ እና የማስታወቂያ ሚኒስትር ፈይሰል ሙHመድ ሳሊህ በትናንትናው ዕለት ተናግረዋል፡፡ የድንበር ማካለል ስራ እስካላለቀ ድረስ ፣ የኢትዮጵያ አርሶአደሮች በኪራይም ይሁን በማንኛውም መልኩ ወደ ሱዳን ግዛት ገብተው እርሻ እንዲያከናውኑ ሀገሪቱ የመስማማት ፍላጎት እንደሌላትም ነው የገለጹት፡፡
በኢትዮጵያ በኩል የድንበሩን ጉዳይ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ከቀደሙት ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መንገድ ፣ ከድንበሩ ጋር በተያያዘ የተቋቋሙና ስራቸውን ያላጠናቀቁ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ስራቸውን እንደገና እንዲጀምሩ በማድረግ መፈታት እንዳለበት ተገልጿል፡፡
በኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ልዑክ በዛሬው ዕለት ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ጋር ትናንት ደግሞ ከሉዓላዊ የሽግግር መንግስቱ ምክትል ሊቀመንበር ሀምዳን ደጋሎ ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
ውይይቱን በተመለከተ የሱዳን መንግስት ባወጣው መግለጫ ፣ ስብሰባው በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል መልካም ጉርብትና ፣ ትብብር እና የጋራ መግባባት መርሆዎችን መሰረት ባደረገ የወንድማማች ግንኙነትን በሚያጎለብት መንፈስ የተካሄደ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ የአሁኑ ስብሰባ ሪፖርት ለመሪዎች ከቀረበ በኋላ ፣ የሚቀጥለው ስብሰባ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ እና ቀኑ በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች እንደሚወሰንም መግለጫው ጠቅሷል፡፡