የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ሉዓላዊ ጽ/ቤቶችን ለመቆጣጠር እየተዋጉ ነው
የሱዳን ግጭት ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ሳይደረስ 103ተኛ ቀኑን ይዟል
ተፋላሚዎች ወታደራዊ እና ስልታዊ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር እያደረጉት ያለው ከባድ ውጊያ ተባብሷል
የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ሉዓላዊ ጽ/ቤቶችን ለመቆጣጠር እየተዋጉ ነው።
የሱዳን ቀውስ 103ተኛ ቀኑን ይዟል። የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በካርቱም ጎዳናዎች ላይ እየተፋለሙ ነው።
ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቆም ውትወታው ቢቀጥልም፤ ረቡዕ በመዲናይቱ የሚገኙትን ወታደራዊ እና ስልታዊ አካባቢዎች ለመቆጣጠር በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ከባድ ውጊያ ተባብሷል።
የአይን እማኞች ለአል ዐይን ኒውስ እንደተናገሩት ጦሩ የፕሬዝዳንቱን ቤተ መንግስት ለማስመለስ እና በመሀል ከተማ የሚገኘውን የመከላከያ ሰራዊት “ጠቅላይ ዕዝ” ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል የአየር ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ሰራዊቱ በኦምዱርማን የሚገኘውን ብሄራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ኮርፖሬሽን ዋና መስሪያ ቤት ለመያዝም እየተዋጋ ነው ብለዋል።
እንደ እማኞች ገለጻ፤ ሰራዊቱ በመድፍ ተኩስ ከካርቱም በስተደቡብ በሚገኘውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ስብስብን ኢላማ አድርጓል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ደግሞ ከከተማዋ በስተደቡብ የሚገኘውን የጦሩ ክፍል እየከበቡ ነው።
ምንጮች ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በባህሪ ከተማ የሚገኘውን “ሲግናል ኮርፕስ”፣ ከካርቱም በስተሰሜን የሚገኘውን “ዋዲ ሰይድና” ወታደራዊ ካምፕን እና በኤል-ኦቤይድ የሚገኘውን “ሼይካን” የአየር ማረፊያ ለመቆጣጠር እየሞከሩ ነው።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ባወጣው መግለጫ እንዳለው “ግጭቱ በካርቱም ፣ባህሪ እና ኦምዱርማን ከተሞች ቀጥሏል” ሲል በዳርፉር (ምዕራብ) እና በኮርዶፋን ግዛቶች (ደቡብ) ጦርነቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ድርጅቱ በሚያዝያ ወር በጦር ሰራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከ 3.5 ሚሊዮን በላይ ሱዳናውያን መፈናቀላቸውን እና መሰደዳቸውን አስታውቋል።