የሱዳን ጦር በአዲስ አበባው የኢጋድ ስብሰባ ያልተሳተፈው ለምንድን ነው?
ኢጋድ የአፍሪካ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይልን ወደ ሱዳን እንዲልክ እጠይቃለሁ ማለቱንም የጦሩ ከፍተኛ አመራሮች ተቃውመውታል
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በትናንቱ የኢጋድ ስብሰባ ተወካዩን ልኮ ተሳትፎ አድርጓል
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ትናንት በአዲስ አበባ ምክክር አድርጓል።
ተፋላሚ ሃይሎቹ በስብሰባው ላይ እንደሚሳተፉ አረጋግጠው የነበረ ቢሆንም፥ ተወካዩን የላከው የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ብቻ ነው።
የሱዳን ጦር ተወካይ አዲስ አበባ ቢገቡም በምክክሩ ላይ አልሳተፍም ማለታቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ የአራትዮሽ (ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ጂቡቲ) ስብሰባውን የሚመሩት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያን ሩቶ በሌላ ካልተተኩ ጦሩ በስብስባው ላይ እንደማይሳተፍ ነው ያስታወቀው።
ፕሬዝዳንቱ ለፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ያደላሉ የሚል ወቀሳ ከሱዳን ጦር ተደጋግሞ ተሰምቷል።
ኢጋድ በበኩሉ የሱዳን ጦር በስብሰባው ላይ እንደሚሳተፍ አረጋግጦ ሳይሳተፍ በመቅረቱ እንዳዘነ ገልጿል።
የፖለቲካ አማካሪያቸውን ወደ አዲስ አበባ የላኩት ጀነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ ጦሩ በስብሰባው ላይ አለመሳተፉን “ሃላፊነት የጎደለው ባህሪ” ብለውታል።
የአራቱ ሀገራት መሪዎች በቀጣይ ተፋላሚ ጀነራሎቹን ፊት ለፊት ለማገናኘት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ባወጡት የጋራ መግለጫ ጠቁመዋል።
ተፋላሚዎቹ በአፋጣኝ ግጭት አቁመው ዘላቂ የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ እንዲደርሱም ነው የጠየቁት።
ኢጋድም የአፍሪካ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይልን ወደ ሱዳን እንዲያሰማራ ሊጠይቅ እንደሚችል ነው ይፋ ያደረገው።
ተጠባባቂ ሃይሉ በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ያሉ ንጹሃንን ለመጠበቅ እና የሰብአዊ ድጋፎች ያለገደብ እንዲንቀሳቀሱ ያግዛል ተብሎም ታምኖበታል።
የሱዳን የቀድሞው ተቃዋሚ እና አሁን ላይ ከጀነራል አልቡርሃን ጋር ወዳጅነት የፈጠሩት ሙባረክ አርዶል ግን እቅዱን “ሱዳንን እንደመውረር ይቆጠራል” ብለው ውድቅ አድርገውታል።
ተጠባባቂ ሃይል የመላክ እቅዱ የውጭ ሃይሎች ወታደራዊ ጣልቃገብነት ለማስፋፋት ያለመ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት።
በትናንቱ የኢጋድ መሪዎች ስብሰባ ላይ የተሳተፉት የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ በበኩላቸው በቀጠናው ያሉ ሀገራት ለየትኛውም ወገን ወታደራዊ ድጋፍ እንዳያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ወታደራዊ ድጋፍና የውጭ ሃይል ጣልቃገብነት ጦርነቱን ከማባባስ ውጭ የሚፈይደው ነገር እንደሌለም በማንሳት።
ከአራት ቀናት በኋላ ሶስተኛ ወሩን የሚይዘው የሱዳን ጀነራሎች ጦርነት 3 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፤ ከ3 ሚሊየን በላይ ሱዳናውያንንም አፈናቅሏል።
ትናንት ስለሀገሪቱ ሰላም ሲመከርም በካርቱም እና በደቡብ ኮርዶፋን ውጊያው መቀጠሉን ነው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዘገበው።