የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች በአዲስ አበባ የፊት ለፊት ውይይት እንደሚያደርጉ ተገለጸ
የሱዳን ብሔራዊ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይል አዛዦች በ10 ቀናት ውስጥ በአዲስ አበባ የፊት ለፊት ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል
ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት የኢጋድ አባል ሀገራት የሱዳንን ጦርነት ለማስቆም የማሸማገል ስራ እንዲሰሩ በኢጋድ መወሰኑ ተገልጿል
የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች በአዲስ አበባ የፊት ለፊት ውይይት እንደሚያደርጉ ተገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የሱዳን ጦርነት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዋነኛው ሲሆን ኢጋድ ከሰሞኑ በጅቡቲ ባካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃዎችን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
ከተጀመረ ሁለት ወራት ያስቆጠረው የሱዳን ጦርነት እልባት እንዲያገኝ ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት ሀገራት የሱዳንን ቀውስ ለመፍታት ጥረቶችን እንዲያደርጉ መወሰኑ ተነስቷል፡፡
በዚህ መሰረትም የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች በአዲስ አበባ የፊት ለፊት ውይይት እና ድርድር በ10 ቀናት ውስጥ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
አምባሳደር መለስ በመግለጫቸው “ኢትጵያን ጨምሮ የአራት ሀገራት መሪዎች ለሱዳን ጦርነት እልባት እንዲያፈላልጉ ተልዕኮ ሰጥቷል፣ ይህ ታሪካዊ ውሳኔ ነው፣ ኢትዮጵያ የሱዳንን ቀውስ ለመፍታት በየጊዜው ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ይህ የኢጋድ ውሳኔ ለኢትዮጵያም ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም (ዶ/ር) የሰላም ጥረት የተሰጠ እውቅና ነው” ብለዋል፡፡
“የሱዳን ተፋላሚ ወገኖችን ፊት ለፊት በማገናኘት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሚና እንዲኖራቸው ተወስኗል” ያሉት አምባሳደር መለስ፥ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊትም የሱዳንን ቀውስ ለመፍታት ጥረት ስታደርግ መቆየቷንም ጠቅሰዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ከትናንት በስቲያ በጅቡቲ ባደረገው የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳንን የሱዳን ጦርነት እንዲቆም መፍትሄ እንዲያፈላልጉ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
በሱዳን ጦርነት ምክንያት የተሻለ ደህንነት ፍላጋ ወደ ኢትዮያ የገቡ ዜጎች ቁጥር ከ45 ሺህ በላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡