የሱዳንን ግጭት ለመፍታት የኢትዮጵያን ጨምሮ የአራት ሀገር መሪዎች ከተፋላሚዎች ጋር ሊመክሩ ነው
መሪዎቹ በቀጣይ 10 ቀናት ከሱዳን ወታደራዊ መሪዎች ጋር በአካል ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሏል
ኬንያ ሊቀ-መንበርነት የሚመራው ስብስብ በሱዳን ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተነግሯል
የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታን ለመፍታት የአራት ሀገር መሪዎች ከካርቱም ተቀናቃኞች ጋር እንደሚወያዩ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) አስታውቋል።
ኢጋድ የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳንን መሪዎች ያካተተ የአራትዮሽ ስብስብ ከጀነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃንና ከጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ጋር ይወያያሉ ብሏል።
መሪዎቹ በቀጣይ 10 ቀናት ውስጥ በአካል እንዲወያዩ መወሰኑንም አስታውቋል።
በ14ኛው የኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ አባል ሀገራት ቀጣናዊ ተቋሙ በምስራቅ አፍሪካ እየሰጠ ያለውን ምላሽ ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ የመከረው ጉባኤው የተለያዩ የውሳኔ ሀሳቦችን አሳልፏል።
የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጉባኤው የኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን መሪዎች ስብስብ ከጀነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን እና ከጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ጋር በቀጣይ 10 ቀናት በመገናኘት ውይይት እንዲያደርግ መወሰኑን ገልጸዋል።
ሀገራቱ ኢጋድን ወክለው በሱዳን ተባብሶ የቀጠለውን ጦርነት ማስቆም እና ሁለቱ ወታደራዊ መሪዎች ጦርነቱን ለማቆም ቁርጠኛ አቋም እንዲወስዱ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይመክራሉ ብለዋል።
በምክክሩ የዜጎችን ህይወት ለመታደግ እንዲሁም እየወደመ ያለውን ንብረትና ሌሎች አይነት ውድመቶችን ማስቆም እንደሚቻልም ተናግረዋል።
በቀጣይ ሁለት ሳምንታት የሰብዓዊ እርዳታ ኮሪዶር መክፈት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ለማድረግ ከስምምነት ላይ መደረሱን የኬንያው ፕሬዝዳንት ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በቀጣይ ሦስት ሳምንታት በሱዳን ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር ሂደት ለመጀመር የመሪዎች ጉባኤው ከስምምነት ላይ መድረሱ ተነግሯል።
ኬንያ በሊቀ-መንበርነት የምትመራው የአራትዮሽ ስብስብ በሱዳን ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።