ዛሬ አዲስ አበባ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ ከንቅናቄው መሪ ጋር እንደሚደራደሩ ይጠበቃል
ዛሬ አዲስ አበባ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ ከንቅናቄው መሪ ጋር እንደሚደራደሩ ይጠበቃል
በአብዱልአዚዝ አልሂሉ የሚመራው የሱዳን ህዝብ ነጻ አውጭ ንቅናቄ የሰሜኑ ክንፍ (SPLM-N) ከሱዳን መንግስት ጋር በአዲስ አበባ ሊደራደር መሆኑን የዲፕሎማቲክ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ቡድኑ ከሰሞኑ በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ ከነበረው የሰላም ስምምነት አፈንግጦ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ የቡድኑ መሪ የሰላም ስምምነቱን ያልፈረመው ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሚቲ) ጋር መነጋገር አልፈልግም በሚል እንደሆነም ነው ምንጮች ለአል ዐይን የገለጹት፡፡
አደራዳሪዎች የነበሩት የደቡብ ሱዳን መሪዎች ደግሞ የቡድኑን መሪ አብዱልአዚዝ አልሂሉን የግድ ከመሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሚቲ) ጋር መደራደር አለብህ ሲሉ ጠይቀው እንደነበር ተገልጿል፡፡
ነገር ግን የንቅናቄው መሪ ከጁባው የሰላም ስምምነት ማፈንገጡ የሚታወስ ሲሆን አሁን ላይ የቡድኑ መሪ አዲስ አበባ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
ዛሬ ደግሞ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ አዲስ አበባ መምጣታቸው እና ከንቅናቄው መሪ ጋር ተገናኝተው እንደሚደራደሩ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች የተገነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩና የንቅናቄውን መሪ በአዲስ አበባ ተገናኝተው እንዲደራደሩ ያመቻቹት ኢትዮጵያና ሌሎች አካላት ናቸው ተብሏል፡፡
ይህ የንቅናቄ ቡድን በሱዳን ብሉናይል እና ደቡብ ኮርዶፋን ግዛቶች የሚንቀሳቀስ ነው፡፡