ፖለቲካ
በሱዳን በተከሰተ የእርስ በእርስ ግጭት 32 ሰዎች ተገደሉ
ግጭቱን ለመቆጣጠር እና ሥርዓት ለማስፈን መንግስት በፖርት ሱዳን ከፍተኛ የጸጥታ ኃይል አሰማርቷል
በሱዳን በተከሰተ የእርስ በእርስ ግጭት 32 ሰዎች ተገደሉ
በምስራቅ ሱዳን ሰሞኑን በተከሰተ የእርስ በእርስ ግጭት 32 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ መንግስት የደህንነት ስራውን አጠናክሯል፡፡
ወትሮውንም ዘላቂ መግባባት በሌላቸው የቤን አሚር እና ኑባ ጎሳዎች መካከል በተከሰተው ግጭት ህይወታቸውን ካጡት 32 ሰዎች በተጨማሪ 98 ሰዎችም ጉዳት እንደደረሰባቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የሱዳን የሀገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው መንግስት ችግሩ በተፈጠረበት የቀይ ባህር ግዛት የሚያከናውነውን የጸጥታ ስራ ያጠናከረ ሲሆን በፖርት ሱዳን ደግሞ ሰዓት እላፊ ታውጇል፡፡
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ እስካሁን 85 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው የተገለጸ ሲሆን በተለይ ግጭቱ ጎልቶ በተከሰተበት ፖርት ሱዳን የመንግስት ጦር ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ከአመት በፊት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አል-ባሽር ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ መረጋጋት የተሳናት ሱዳን በተለያዩ ግዛቶቿ በተለያየ ጊዜ የሚከሰቱ ግጭቶች እና የኢኮኖሚ ቀውስ ፈተና ሆነውባታል፡፡