የሱዳን ጠ/ሚ/ር ሀምዶክ እና የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሚኒስትር ምኑቺን በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ተወያዩ
አሜሪካ የግብጽ ወገንተኛ መሆኗን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ገልጻለች
በግድቡ ዙሪያ በሶስቱ ሀገራት መካከል ስምምነት እንዲደረስ ሱዳን ጥረቷን እንደምትቀጥል ጠ/ሚ/ር ሀምዶክ ገልጸዋል
የሱዳን ጠ/ሚ/ር ሀምዶክ እና የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሚኒስትር ምኑቺን በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በስልክ ተወያዩ
የአሜሪካው የግምጃ ቤት ኃላፊ ስቴቨን ምኑቺን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር ስልክ ደውለው በግድቡ ዙሪያ ዉይይየት ማድረጋቸውን አል ዐይን አረብኛ ዘግቧል፡፡ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረገው ድርድር የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ ዉይይት ማድረጋቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ማክሰኞ ዕለት በተደረገው በዚህ ዉይይት በግድቡ ዙሪያ በሶስቱ ተደራዳሪ ሀገራት ማለትም በኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል ስምምነት እንዲደረስ ሱዳን የምታደርገውን ጥረት ስቴቨን ምኑቺን ማድነቃቸው ተገልጿል፡፡
ሱዳን በሶስቱ ሀገራት መካከል ስምምነት እንዲደረስ የጀመረችውን ጥረት እንደምትቀጥል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትረ አብደላ ሀምዶክ ፣ አሜሪካ ለምታደርገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ይሁንና በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በአሜሪካ የግምጃ ቤት ሚኒስትሩ መካከል ስለ ተደረገው ዝርዝር ዉይይት የተባለ ነገር የለም፡፡
የአሜሪካው የግምጃ ቤት ሚኒስትር “ስቴቨን ምኑቺን ግብጽን በመወገን" የቆሙ ግለሰብ” ስለ መሆናቸው ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ አስታውቃለች፡፡
በሶስቱ ሀገራት መካከል ከዚህ ቀደም አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በተገኙበት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ኢትዮጵያ ባለፈው የካቲት ወር በዋሺንግተን ዲ.ሲ በተዘጋጀው የመጨረሻ ድርድር ባለመሳተፏ ሳይቋጭ መቋረጡ ይታወሳል፡፡
“አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በሶስቱ ሀገራት ድርድር ላይ በታዛቢነት ከመሳተፍ ባለፈ በሂደት የስምምነት ሰነድ እስከማዘጋጀት የደረሰ ተሳትፎ በማድረግ ለግብጽ ወገንተኝነታቸውን አሳይተዋል” በሚል ኢትዮጵያ ቅሬታዋን አቅርባለች፡፡ የአሜሪካ ግምጃ ቤት አሜሪካን በመወከል ያዘጋጀው የመጨረሻ የስምምነት ሰነድ በግብጽ ሲፈረም ኢትዮጵያና ሱዳን ዉድቅ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
የግድቡን የዉሃ ሙሌትም በአሁኑ የክረምት ወቅት እንደምትጀምር ኢትዮጵያ ይፋ አድርጋለች፡፡
ይሁን እንጂ በስቴቨን ምኑቺን የሚመራው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ባወጣው መግለጫ በሶስቱ ሀገራት መካከል የመጨረሻ ስምምነት ሳይደረስ የዉሃ ሙሌቱ እንዳይጀመር ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡
የዋሽንግተኑ ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያሳድር የሚጠይቅ ደብዳቤ ግብጽ ለድርጅቱ የላከች ሲሆን የድርጅቱ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሶስቱ ሀገራት አለመግባባታቸውን በ2015ቱ የካርቱም የመርሆች ስምምነት መሰረት በድርድር እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
በሱዳን አነሳሽነት ዳግም የተጀመረው ድርድር መግባባት ባልተደረሰባቸው የህግ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ዉሳኔ ከተላለፈ በኋላ እንዲቀጥል በሶስቱ ሀገራት ተደራዳሪዎች መካከል ስምምነት ቢደረስም ግብጽ በድጋሚ የህዳሴ ግድቡን ጉዳይ “የዓለም አቀፍ ስጋት” ጉዳይ አድርጋ ወደ ተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች፡፡ ለግብጽ አቤቱታ የምላሽ ደብዳቤ የጻፉት የኢትዮጵያ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ፣ ግብጽ ለድርድሩ መልካም ፍላጎት እንደሌላት እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሰላም መደፍረስ ቢያጋጥም እንኳን ተጠያቂዋ ግብጽ መሆኗን በደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡
ግብጽ የህዳሴ ግድቡ በየዓመቱ የማገኘውን የዉሃ መጠን ይቀንስብኛል የሚል ስጋት ሲኖራት ኢትዮጵያ ደግሞ በታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ የግድቡን ግንባታና የዉሃ ሙሌት እንደምታከናውን በተደጋጋሚ መግለጿ ይታወቃል፡፡