የሱዳን የመረጃ መንታፊዎች ጀነራል ዳጋሎን ተቀብላ ባስተናገደችው ኡጋንዳ ላይ የሳይበር ጥቃት ለማድረስ መሞከራቸው ተገልጿል
ጦርነት ውስጥ ከገባች 10ኛ ወሯን ባስቆጠረችው ሱዳን በርካታ አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ተነገረ።
የኢንተርኔት ነጻነት ተቆጣጣሪው ኔትብሎክስ በሱዳን የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን በኤክስ ገጹ ላይ አስፍሯል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል አዛዥ ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ)ን ተቀብላ ማስተናገዷ ያስቆጣው የሱዳን የመረጃ መንታፊ ቡድን በኡጋንዳ የሳይበር ጥቃት ለማድረስ መሞከሩም ተዘግቧል።
በዚህም የኡጋንዳ ቴሌኮም እና ኤምቲኤን አገልግሎታቸውን በሚገባ ማቅረብ አልቻሉም ብሏል ኔትብሎክስ።
በካምፓላ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ግን የኢንተርኔት መቆራረጥ ችግር እንዳላጋጠመው ገልጿል።
በሱዳን ካለፈው አርብ ጀምሮ የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት ፈታኝ መሆኑን ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን፥ ችግሩ እየተባባሰ መሄዱም ተጠቅሷል።
የሱዳን መንግስት መገናኛ ብዙሃን ለኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጡ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉን ተጠያቂ አድርጓል።
አርኤስኤፍ በበኩሉ በአብዛኛው በተቆጣጠራቸው የዳርፉር፣ ኮርዶፋን፣ ካርቱምና አል ጃዚራህ ክልሎች የመገናኛ ስርአት እንዲወድሙ አድርጎ ኢንተርኔት ያቋረጠው የሱዳን ጦር ነው በሚል መክሰሱን ሱዳን ትሪቡን አስነብቧል።
ኔትብሎክስ ባወጣው መረጃ በሱዳን ዋነኛ የኢንተርኔት አቅራቢ ዛይን “በአብዛኛው ስራ አቁሟል” ብሏል።
ዛይን በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫም “እጅግ ከባድ እና አደገኛ” በሆነ ሁኔታ ስራውን እያካሄደ መሆኑንና የኔትወርክ መቆራረጡ ከቁጥጥሩ ውጭ መሆኑን ነው ያስታወቀው።
የደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን ሱዳን እና የሱዳን መንግስት ንብረት የሆነው ሱዳኒም ከአርብ ጀምሮ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማቅረብ መቸገራቸው ተገልጿል።
10ኛ ወሩን በያዘው ጦርነት ላይ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ለሱዳናውያን ሌላ ፈታኝ ጉዳይ ሆኗል የተባለ ሲሆን፥ ጦርነቱ በቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይ ከባድ ጉዳት እንዳደረሰ ማሳያ ተደርጎ ቀርቧል።
ጦርነቱ ከ9 ሚሊየን ሰዎች በላይ ሰዎችን ማፈናቀሉን የጠቀሰው የመንግስታቱ ድርጅት ከ25 ሚሊየን በላይ (የሱዳን ግማሽ ህዝብ) እርዳታ ጠባቂ መሆኑን ገልጿል።
ድርርጅቱ በቅርቡም ለሱዳን ፈጣን የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ አለማቀፉ ማህበረሰብ የ4 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።