ደቡብ ሱዳን ጅን የተሰኘው የአልኮል መጠጥ እንዳይሸጥ አገደች
ሀገሪቱ አልኮል መጠጡን ያገደችው መጠጡን የጠጡ ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ነው
በደቡብ ሱዳን ለገና እና አዲስ ዓመት በዓል ጅን አልኮልን የጠጡ በርካታ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል ተብሏል
ጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን ጅን የተሰኘውን ደረቅ አልኮል መጠጥ እንዳይሸጥ እና እንዳይጠጣ አግዳለች፡፡
የማዕከላዊ ኢኳቶሪያ ግዛት ሮያል ጅን የተሰኘውን ታዋቂ የአልኮል መጠጥ ያገደችው ምርቱን የወሰዱ ዜጎች እየሞቱ ነው በሚል ነው፡፡
በደቡብ ሱዳን በተለይም ወጣቶች ሮያል ጅን ወይም በቅጽል ስሙ ማኪዌ የተሰኘው ደረቅ አልኮል መጠጥ አብዝተው ይጠቀሙታል ተብሏል፡፡
ይህን አልኮል የወሰዱ ሰዎች ብዙ እንዲያወሩ ወይም እንዲለፈልፉ ያደርጋል የተባለ ሲሆን ማኩዌ የሚለውን ቅጽል ስም ያገኘው ብዙ በማውራት ይታወቃሉ በሚባሉት የቀድሞ የሀገሪቱ ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ሚካኤል ማኩዌ ስም ተሰይሟል፡፡
ፕሬዝደንቱን የሚያሳይ ያልተገባ ቪዲዮ ለቀዋል የተባሉት የደቡብ ሱዳን ጋዜጠኞች ታሰሩ
በደቡብ ሲዳን በዓላት አካባቢ የአልኮል ገበያ ይደራል የተባለ ሲሆን በብዛት ከሚሸመቱ የአልኮል መጠጦች ውስጥ አሁን የታገደው ሮያል ጅን ወይም ማኩዌ ዋነኛው ነው፡፡
ይህን መጠጥ የጠጡ ወጣቶች እናቶቻቸውን ሳይቀር በገጀራ እየመቱ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የሀገሪቱ አንግሊካን ቤተ ክርስቲያን መግስት የወሰደውን እርምጃ እንደሚደግፍ ገልጾ ውሳኔውን እንዲተገብር ጠይቋል፡፡
በተለምዶ ማኩዌ የተሰኘውን ይህን አልኮል መጠጥ የሚያመርተው ሮያል ጅን ኩባንያ በቀጣይ በደንበኞች እጥረት ሊዘጋ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡