በሀገሪቱ በኩፍኝ ወረርሽኝ በመጠለያ ጣቢያ የ13 ህጻናት ህይወት ማለፉ ተነገረ
ድንበር የለሽ ሀኪሞች እንዳስታወቁት በሱዳን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ (ካምፕ) ውስጥ የኩፍኝ ወረርሽኝ ተቀስቅሷል።
በሱዳን ዋይት ናይል ግዛት ካምፕ ውስጥ በወረርሽኙ 13 ህጻናት መሞታቸውን ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ ድርጅት አስታውቋል።
ድርጅቱ በትዊተር ገጹ ላይ "በየቀኑ በኩፍኝ የተጠረጠሩ የታመሙ ህጻናትን እየተቀበልን ነው፤ አብዛኛዎቹ ችግሮች የተወሳሰቡ ናቸው" ብሏል።
በሱዳን በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ሸሽተው ወደ ካምፑ ሰዎች እየፈሰሱ ነው ተብሏል።
ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን በነጭ አባይ ሁለት ክሊኒኮች አሉት ሲል ቪኦኤ ዘግቧል።
ድርጅቱ በሰኔ ወር ከሦስት ሽህ በላይ ታማሚዎች እንደነበሩት ገልጾ "እርዳታን ማሳደግ፣ እንደ ክትባቶች፣ የተመጣጠነ ምግብ ድጋፍ፣ መጠለያ፣ ውሃ እና የንጽህና መጠበቂያ ያሉ አገልግሎቶች መጨመር አለባቸው" ብሏል።