በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በተፈጸመ የአየር ጥቃት 5 ህጻናትን ጨምሮ 17 ሰዎች ተገደሉ
የሱዳን ጦር የአየር ጥቃቶችን ከፍ አድርጎ በርካታ የመኖሪያ ሰፈሮችን እየደበደበ ነው ተብሏል
ጦሩ ዜጎች ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከያዛቸው ቤቶች እንዲርቁ አስጠንቅቋል
በሱዳን ዋና ከተማ የደረሰ የአየር ጥቃት ሰላማዊ ዜጎችን ገድሏል።
በደቡባዊ ካርቱም ማዮ አካባቢ አምስት ህጻናትን ጨምሮ 17 ሰዎች መሞታቸውን እና 25 ቤቶች መውደማቸውን ጤና ጥበቃ ሚንስቴር ገልጿል።
በከተማዋ በርካታ አካባቢዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙን ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን፤ አደራዳሪዎች ተፋላሚ ወገኖችን ወደ አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ሲገፋፉ ውለዋል።
በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ሁለቱም ወገኖች ግልጽ የሆነ ጥቅም ሳያገኙ ወደ ሦስተኛ ወሩ እየገባ ነው።
በጦርነቱ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሱዳናውያንን ከቀያቸው መፈናቀላቸውን እና በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።
ጦሩ በካርቱም እና በአጎራባች ከተሞች የአየር ኃይል የበላይነት ያለው ሲሆን፤ አር.ኤስ.ኤፍ በመባል የሚታወቀው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ግን በመኖሪያ ሰፈሮች ውስጥ ይንቀሳቀሳል።
አርብ እና ቅዳሜ ጦሩ የአየር ጥቃቶችን ከፍ አድርጎ በርካታ የመኖሪያ ሰፈሮችን እየመታ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
በጦር ኃይሉ በተለቀቀ ንግግር ላይ ከፍተኛ ጄኔራል ያሲር አል-ታታ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከያዛቸው ቤቶች እንዲርቁ አስጠንቅቀዋል።
ምክንያቱም "በዚህ ጊዜ የትም እናጠቃቸዋለን። በእኛ እና በእነዚህ አማፂዎች መካከል ጥይት ነው ያለው" ሲሉ ተናግረዋል።