ሱዳን፥ ኬንያ "የሱዳንን ግጭት የሁለት ጄኔራሎች ፍልሚያ ነው" ማለቷን በጽኑ እቃወማለሁ ብላለች
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በሀገሪቱ ውስጥ ስላለው ክስተት በኬንያ የተጠራውን የአራትዮሽ ስብሰባ እንደሚቃወም አስታውቋል።
የሱዳን መንግስት ሰኞ ከሰአት በኋላ ኬንያ የጠራችውን ስብሰባ ይቃወማል ነው ያለው ሚኒስቴሩ።
የኬንያ መንግስት "የሱዳንን ግጭት የሁለት ጄኔራሎች ፍልሚያ ነው" የሚል አስተያየት መስጠቱ ነው ካርቱምን ያስቆጣው።
የሱዳን መንግስት "ያለፈቃዱ" የሚካሄደውን ስብሰባ እንደሚቃወመው እና ዉጤቱ እንደማያሳስበው በውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ በኩል አስታውቋል።
ሱዳን በኢጋድ የተሰየመውንና በኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የሚመራውን ኢትዮጵያን ያካተተ የአራት ሀገራት መሪዎች አሸማጋይ ኮሚቴ እንደማትቀበል ከዚህ ቀደም አስታውቃለች።
ተቃውሟንም ለኢጋድ አመልክታ ምላሽን እየጠበቀች እንደሆነ ተናግራለች።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የኬንያ የሽምግልና አያያዝ የኢጋድን መርሆች ይቃረናል ብሏል።
ሪያድ እና ዋሽንግተን ቅዳሜ አመሻሽ የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በመላ ሀገሪቱ ከእሁድ ጀምሮ የሚተገበር የ72 ሰዓታት የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጋቸውን መግለፁ ይታወሳል።