አርኤስኤፍ በደቡብ ምስራቅ ሱዳን ወሳኝ ከተማ ተቆጣጥሬያለው አለ
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ የሴናር ግዛት ዋና ከተማ የሆነችውን ሲንጋ ከሱዳን ጦር ማስለቀቁን ነው ያስታወቀው
የሱዳን ጦር በበኩሉ በከተማዋ ውጊያው መቀጠሉን ገልጿል
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል በሀገሪቱ ደቡብ ምስራቃዊ ክፍል የምትገኝ ወሳኝ ከተማን መቆጣጠሩን አስታወቀ።
አርኤስኤፍ የሴናር ግዛት ዋና ከተማዋን ሲንጋ ነው መቆጣጠሩን የገለጸው።
ቡድኑ “በሲንጋ የሚገኘውን 17ኛ እግረኛ ክፍለጦር ነጻ አውጥተነዋል” ሲል በኤክስ(ትዊተር) ገጹ ላይ አስፍሯል።
ፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ሲንቀሳቀሱ መመልከታቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
ጦርነቱ ለቀናት በመቀጠሉም በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው እየወጡ መሆናቸውን ነው ዘገባው የጠቆመው።
የሴናር ግዛት ጦርነትን የሸሹ ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች መኖሪያ ክልል ሲሆን፥ ማዕከላዊውን ሱዳን በሱዳን ጦር ቁጥጥር ስር የሚገኙ የደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች ያገናኛል።
የሱዳን ጦር በበኩሉ ወታደሮቹ አሁንም ድረስ በሲንጋ ከተማ እንደሚገኙ በመጥቀስ ውጊያው መቀጠሉን አስታውቋል።
በሚያዚያ ወር 2023 የተቀሰቀሰው የሱዳን ጀነራሎች ጦርነት በ10 ሺህ የሚቆጥሩ ሱዳናውያንን ህይወት ቀጥፏል፤ ሚሊየኖችም በሀገር ውስጥና ድንበር አቋርጠው ለመሰደድ ተገደዋል።
የጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና የጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ፍልሚያ 48 ሚሊየን ህዝብ ያላትን ሱዳን በአለማችን ከባድ የሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ካሉ ሀገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ አስቀምጧታል።
የመዲናዋን ካርቱም አብዛኛው ክፍል፣ አል ጀዚራ ግዛት፣ አብዛኛውን የዳርፉር እና ኮርዶፋን አካባቢ የተቆጣጠረው የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምስራቅና ምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍልም ድል እየቀናው መሆኑን የቪኦኤ ዘገባ ያሳያል።
በሱዳን ጦር ስር የምትገኘውንና የሰሜን ዳርፉር መናገሻዋን ኤል ፋሸር ለመቆጣጠርም ውጊያው መቀጠሉን ነው የዘገበው።
ሃሜቲ የሚመሩት አርኤስኤፍ የሲንጋ ከተማን መቆጣጠር የሱዳን ጦርና የመንግስታቱ ድርጅት ድርጅቶች ወደሚገኙባት ፖርት ሱዳን ለሚያደርገው ጉዞ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል።
ኦማር ሀሰን አልበሽርን ለመጣል የተባበሩት አልቡርሃን እና ዳጋሎ ልዩነታቸውን በንግግር ለመፍታት አለመፈለጋቸው በቋፍ ውስጥ የነበረውን የሱዳን ህዝብ ለከፋ ስቃይ መዳረጉን ቀጥሏል።
የመንግስታቱ ድርጅት ከሶስት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫም 26 ሚሊየን የሚጠጉ ሱዳናውያን ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር ገጥሟቸዋል ማለቱ የሚታወስ ነው።