የሱዳን ተፋላሚዎች በህጻናት ላይ ጥቃት በማድረስ በዓለምአቀፍ ጥቁር መዝገብ ውስጥ ተካተቱ
ሪፓርቱ በሱዳን ውስጥ 1721 ጥሰቶች መፈጸማቸውን አረጋግጧል።
የተመድ ዋና ጸኃፊ በህጻናት ላይ ግድያን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶች ፈጽመዋል ያሏቸውን የእስራኤል ጦር፣ የሀማስ ታጣቂን እና የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን አጥበቀው ኮንነዋል
የሱዳን ተፋላሚዎች በህጻናት ላይ ጥቃት በማድረስ በዓለምአቀፍ ጥቁር መዝገብ ውስጥ ተካተቱ።
የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በ2023 በህጻናት ላይ ግድያን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶች ፈጽመዋል ያሏቸውን የእስራኤል፣ የሀማስ እና የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን አጥበቀው ኮንነዋቸዋል፤ በህጻናት ላይ የመብት ጥሰት አድራሾች አመታዊ አለምአቀፍ ዝርዝር ውስጥም አካተዋቸዋል።
ዋና ጸኃፊው ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፓርት የእስራኤል እና የሱዳን የታጠቁ ኃይሎች ትምህርት ቤቶችን እና ሆስፒታሎችን ማጥቃቸውን፣ ሀማስ እና እስላማዊ ጅሀድ ደግሞ ተማሪዎችን ማገቱን ማውገዛቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ከባለፈው ሚያዝያ ጀምሮ ከሱዳን ጦር ጋር እየተዋጋ ያለው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጦር ህጻናትን ለጦርነት በመመልመል እና በመጠቀም፣አስገድዶ በመድፈር ሌሎች ወሲባዊ ጥቃቶችን በመፈጸም እንዲሁም ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎችን በማጥቃት ተወንጁሏል።
በጉተሬዝ የህጻናት እና የትጥቅ ግጭት ተወካይ በሆኑት ቪርጂኒያ ጋምባ የቀረበው ሪፓርት ስድስት ከባድ ጥሰቶችን ማለትም ግድያን እና አካል ማጉደልን፣ ወሲባዊ ጥቃትን፣ እገታን፣ ምልመላ እና መጠቀምን፣እርዳታ መከልከልን እና ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎችን ማጥቃትን የሚሸፍን ነው።
በሪፓርቱ የመብት ጥሰት ፈጽማዋል የተባሉት ኃይሎች በዝርዝሩ ውስጥ እንዲካተቱ የተደረገው ተፋላሚ ኃይሎች ህጻናትን ከጥቃት እንዲጠብቁ ጫና ለማሳደር ነው ተብሏል። ሪፓርቱ የሚቀርበው በተመድ በተረጋጡ መረጃዎች ላይ ብቻ ተመርኩዞ ነው።
"በ2023 በግጭት ውስጥ ባሉ ህጻናት ላይ የደረሰው ጥቃት አስደንጋጭ ወደሚባል 21 በመቶ ከፍ ብሏል" ሲል ሪፓርቱ ገልጿል።
እንደሪፓርቱ " የግድያ እና አካል የማጉደል ሁነቶችም በ35 በመቶ ጨምረዋል።
"በእስራኤል፣በተወረረ የፍልስጤም ግዛት፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በሚያንማር፣ በሶማሊያ፣በናይጀሪያ እና በሱዳን ከባድ ጥሰቶች መፈጸማቸው ተረጋግጧል"ያለው ሪፓርቱ የማረጋገጥ ስራውን "እጅግ ከባድ" ሲል ገልጾታል።
እንደሪፓርቱ ከሆነ የእስራኤል ጦር እና የጸጥታ ኃይል 5698 ጥሰቶችን፣ ሀማስ 116 እንዲሁም የፍልስጤም እስላማዊ ጅሀድ ደግሞ 21 ጥሰቶችን ፈጽመዋል።
ሪፓርቱ በሱዳን ውስጥ 480 ግድያዎችን እና በአብዛኛው በተኩስ ልውውጥ የተፈጠሩትን 764 አካል ማጉደሎችን ጨምሮ 1721 ጥሰቶች መፈጸማቸውን አረጋግጧል።
የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የመብት ጥሰት በማድረስ እንደኛቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ ያደርጋሉ፤ የመብት ጥሰት አልፈጸምንም ሲሉም ይደመጣሉ።