በሱዳን ከጥይት በበለጠ ረሃብ በርካቶችን ለሞት እየዳረገ ነው - ሃምዶክ
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሱዳን ከጦርነት አዙሪት እንድትወጣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል
በሱዳን ከ25 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለረሃብና ቸነፈር መዳረጋቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ገልጿል
በሱዳን ጦርነት ምክንያት በረሃብ የሚያልቀው ህዝብ ቁጥር አሳሳቢ መሆኑን የቀድሞው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ተናገሩ።
ሃምዶክ ከዘናሽናል ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሱዳናውያን በጦርነቱ ምክንያት “ከሚታሰበው በላይ ስቃይ” ውስጥ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።
ከ10 ሚሊየን በላይ ሰዎች በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉባት እና ከ25 ሚሊየን በላይ ህዝብ በረሃብና ቸነፈር ውስጥ የሚገኙባትን ሱዳን ቀውስ ለመፍታት ፈጣን እርምጃ ያሻል ብለዋል።
በሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ ኤል ፋሸር ለሳምንታት የዘለቀ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን ያነሱት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር፥ የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በመላ ሀገሪቱ እያካሄዱት ያለው ጦርነት በፖለቲካዊ ንግግር እንዲቆም ጥረት እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
የሱዳን የሲቪል ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ጥምረት (ታቃዱም) ሊቀመንበሩ ሃምዶክ ከሰሞኑ በኖርዌይ መዲና ኦስሎ በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባተኮረው ምክክር ተሳትፈዋል።
ነጻነቷን ከማወጇ አስቀድሞ ከፈረንጆቹ 1955 ጀምሮ ጦርነት የተፈራረቀባት ሱዳን፥ ከ2 ሚሊየን በላይ ዜጎቿን በእርስ በርስ ጦርነት አጥታለች፤ በዳርፉር የዘር ፍጅትም ከ300 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ህይወታቸው መቀጠፉን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል።
ካርቱም በየጊዜው በሚቀያየር ህገመንግስት እና ወታደራዊ መንግስት መመራቷ ከጦርነት አባዜ እንዳትወጣ እንዳደረጋትም ነው አብደላ ሃምዶክ ለዘናሽናል የተናገሩት።
ሱዳንን ለ30 አመታት የመሩት ኦማር አል በሽር ከስልጣን እንደተወገዱ ከ2019 እስከ 2021 ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ሃምዶክ፥ በተፋላሚዎቹ ጀነራሎች ላይ ጫና ለማሳደርና የሲቪል አስተዳደር እንዲቋቋም እየሰሩ ነው።
በጥቅምት ወር 2023 ባቋቋሙት የሲቪል ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ጥምረት (ታቃዱም) ስርም የተለያዩ ሲቪል ተቋማት እና የፖለቲካ ሃይሎችን ለማቀራረብ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
የመጀመሪያ ስብሰባቸውንም በአዲስ አበባ አድርገው ባለፈው ወርም ከ600 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት ምክክር ማድረጋቸው ይታወሳል።
የሱዳን ዲያስፖራዎችን እና የሲቪል ተቋማትን እያስተሳሰረ ያለው “ታቃዱም” ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሚቲ) ልዩነታቸውን በፖለቲካዊ ንግግር እንዲፈቱና ሱዳን ከጦርነት አዙሪት እንድትወጣ የጀመረውን ጥረት አለማቀፉ ማህበረሰብ እንዲደግፍ ሃምዶክ ጠይቀዋል።
ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር የጀመረው የሱዳን ጀነራሎች ፍልሚያ በንግግር እንዲቆም ሳኡዲ አረቢያ እና አሜሪካ በጂዳ ካደረጉትና በአጭሩ ከተቀጨው ሙከራ ውጭ እስካሁን ተስፋ ሰጪ ንግግር አልተካሄደም።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) እና የሱዳን ጎረቤቶች ተፋላሚ ጀነራሎቹን ፊት ለፊት ለማገናኘት ያደረጉት ሙከራም ሳይሳካ መቅረቱ ይታወቃል።