የአውሮፓ ህብረት ከሱዳን ጦርነት ጋር በተያያዘ በ6 ሰዎች ላይ ማዕቀብ ጣለ
የቀድሞው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ማዕቀብ ከተጣለባቸው ዝርዝር ውስጥ ተካቷል
ሱዳንን ለ30 አመታት ለሚጠጋ ጊዜ ያስተዳደሩት ኡመር ሀሰን አልበሽር በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሀገሪቱ ፓለቲካዊ ቀውስ ገብታለች
የአውሮፓ ህብረት ከሱዳን ጦርነት ጋር በተያያዘ በ6 ሰዎች ላይ ማዕቀብ ጥሏል።
የአውሮፓ ህብረት በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር መካከል እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ በስድስት ሰዎች ላይ ማዕቀብ መጣሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
ማዕቀቡ ከተጣለባቸው ውስጥ በዳርፉር ያለውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር የሚመራው እና የአውሮፓ ምክር ቤት ለተፈጸመው ግፍ እና ጎሳ ተኮር ግጭት እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ኃላፊነት ይወስዳሉ ያለው ጀነራል ይገኝበታል።
ከዘህ በተጨማሪም የፈጥኖ ጀራሽ ኃይሎች የፋይናንስ አማካሪ እንዲሁም ከምዕራብ ዳርፉር ውስጥ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው የመሀሚድ ጎሳ መሪ የማዕቀብ ሰለባ ሆነዋል።
በሱዳን ጦር በኩል ደግሞ ማዕቀቡ በመከላከያ ኢንዱስትሪ ሲስተም ዳሬክተሩ እና በሱዳን አየር ኃይል አዛዥ ላይ ማነጣጠሩን የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ገልጿል።
የቀድሞው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ማዕቀብ ከተጣለባቸው ዝርዝር ውስጥ ተካቷል።
ማዕቀብ የተጣለባቸው ስድስቱ ግለሰቦች በ27ቱ የአውሮፓ ህብረት ያላቸው ሀብት እንዳይንቀሳቀስ እና ራሳቸውም ወደ እነዚህ ሀገራት እንዳይንቀሳቀሱ እግድ ተጥሎባቸዋል።
የአሜሪካ መንግስት የሱዳን ተፋላሚዎች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ብያኔ ማሳለፉ የሚታወሰ ነው።
ሱዳንን ለ30 አመታት ለሚጠጋ ጊዜ ያስተዳደሩት ኡመር ሀሰን አልበሽር በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሀገሪቱ ፓለቲካዊ ቀውስ ገብታለች።
የአል በሽርን ከስልጣን መወገድ ተከትሎ ወታራዊ እና ሲቪል አስተዳደር ያካተተ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ የነበረ ቢሆንም ወታደሮቹ የሲቪል አስተዳደሩን የሚመሩንትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክን በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን አስወግደዋል።
መፈንቅለ መንግስቱን የመሩት ሁለቱ ጀነራሎች መካከል ጸብ ተፈጥሮ ባለፈው አመት ሚያዝያ ወር የተቀሰቀሰው ጦርነት እስካሁን አልቆመም።
በጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ ሚሊዮኖች ደግሞ ከቀያቸው ተሰድደዋል።