የሱዳኑ ሄሜቲ አስቸኳይ ተኩስ አቁም ለማድረግ ከጦሩ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ
በቅርብ ቀናት ሁለቱ ኃይሎች በካርቱም እያደረጉ ያሉት የከባድ መሳሪያ ተኩስ ልውውጥ ጨምሯል
ግጭቱን ለማቆም መሰረት ይሆናል የተባለውን 'የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን' በመፈረም፣ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ግጭቱን ለማቆም ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል ተብሏል
የሱዳኑ ሄሜቲ አስቸኳይ ተኩስ አቁም ለማድረግ ከጦሩ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን የሚመሩት ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ወይም ሄሜቲ አስቸኳይ ተኩስ አቁም ለማድረግ ከሱዳን ጦር ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከታኳደም የሲቪል ጥምረት ጋር ዲክላሬሽን የፈረሙት ሄሜቲ ከሱዳን ጦር ጋር በሚደረግ ንግግር አስቸኳይ እና ያለቅድመ ሁኔታ ተኩስ ለማቆም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘጠኝ ወራትን ያስቆጠረው የሱዳን ጦርነት፣ በአለም ትልቅ የሚባል የስደት ቀውስ እንዲፈጠር፣ መሰረተልማት እንዲወድም እና የረሀብ አደጋ እንዲያንዣብብ ምክንያት ሆኗል።
አሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያደረጉት ጥረት እስካሁን ያልተሳካ ሲሆን ቀደም ሲል ንጹሃንን ለመጠበቅ የተደረሰው ስምምነትም ተግባራዊ አልሆነም።
ግጭቱን ለማቆም መሰረት ይሆናል የተባለውን 'የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን' በመፈረም፣ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ግጭቱን ለማቆም ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል ተብሏል።
የተፈናቀሉ ሚሊዮኖችን ለመመለስ፣ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመፍጠር እና የሲቪል አስተዳደርን በሰላም ንግግሩ ለማሳተፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት የገለጹት ሄሜቲ "ጦሩ ይህን ሰነድ የሚቀበለው ከሆነ እኔ ወዲያውኑ እፈርማለሁ" ብለዋል።
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የተሻለ ድል ያገኙት እና በአሜሪካ የሰብአዊ መብት ጥሰት ክስ የሚቀርብባቸው ሄሜቲ ዲክላሬሽኑን ለመተግበር ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆኑ ግልጽ አይደለም።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው አንዳንድ ቦታዎች ፖሊስ እና ገበያ መመለሳቸውን ይፋ ቢያደርጉም፣ ነዋሪዎች እና የሰብአዊ መብት ሰዎች ግን ወታደሮች ዘረፋ እና እስር እና አልፎ አልፎ ግድያ እንደሚፈጽሙ ገልጸዋል።
በቅርብ ቀናት ሁለቱ ኃይሎች በካርቱም እያደረጉ ያሉት የከባድ መሳሪያ ተኩስ ልውውጥ ጨምሯል።
መጠነሰፊ የአየር ጥቃት እየፈጸመ ያለው የሱዳኑ ጦርም የጦር ወንጀል በመፈጸም በአሜሪካ ክስ ቀርቦበታል።
የታኳደም ሲቪል ጥምረት መሪ እና የቀድሞው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የሱዳን ጦርን መጋበዛቸውን እና ቀና መልስ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
ሀምዶክ ከስልጣን የተነሱት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና በሱዳን ጦር ትበብር ነበር።