ጄነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ አዲስ አበባ ሲደርሱ አቶ ደመቀ መኮንን አቀባበል አድርገውላቸዋል
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊት አዛዥ ጀነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሃሜቲ) አዲስ አበባ በዛሬው እለት አዲስ አበባ ገብተዋል።
ጀነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሃሜቲ) አዲስ አበባ ሲደርሱም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አቀባበል እንዳደረጉላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒቴር አስታውቋል።
ካሳለፍነው ሚያዚያ ወር ጀምሮ ከሱዳን ብሔራዊ ጦር ጋር እየተዋጉ ያሉት የፈጥኖ ደራሽ ሀይል አዛዥ ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ወይም ሄመቲ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት በኡጋንዳ ቆይታ አድርገው ነበር።
ጀነራል ሄመቲ ከኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ ጋር እንደተወያዩ የተገለጸ ሲሆን ጦርነቱን በውይይት መፍታት ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደተነጋገሩም ፕሬዝዳንቱ በኤክስ አካውንታቸው ላይ አስፍረዋል።
ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒም ሱዳናዊን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ገልጸው ኡጋንዳ የሱዳን ጦርነት እንዲቆም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ለጀነራል ሄመቲ ነግረዋቸዋልም ተብሏል።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የሱዳን ጦርነት እንዲቆም ተፋላሚ ወገኖችን ፊት ለፊት ከማገናኘት ባለፈ የኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መሪዎች መፍትሄ እንዲያፈላልጉ መሾሙ ይታወሳል።
ኢጋድ የሱዳን ብሄራዊ ጦር አዛዥ ጀነራል አልቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች አዛዥ ጀነራል ሄመቲን ፊት ለፊት እንዲገናኙ ለዛሬ ቀጠሮ የነበረው ቢሆንም ይህ ፕሮግራምን ወደ ጥር ወር አሸጋግሮታል፡፡
ዘጠኝ ወር የሞላው የሱዳን ጦርነት መቋጫ እንዲያገኝ እና ወደ ስምምነት እንዲመጣ የተለያዩ አካላት ተጽዕኖ በማድረግ ላይ ቢሆኑ በጀነራል ሄመቲ የሚመራው ጦር የሱዳን ጦር ማዘዣዎችን በመቆጣጠር ላይ ይገኛል፡፡
የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ጀነራል አልቡርሃን በበኩላቸው የጦሩ ቁልፍ ማዘዣዎች በቀላሉ በፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች እንዲያዝ ያደረጉ አመራሮችን እንደሚቀጡ መዛታቸው ይታወሳል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ጀነራል ሄመቲ ከኡጋንዳ ጉብኝታቸው በኋላ ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ ተብሎ ይገመታል፡፡