የሱዳን ጦር ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎን ተቀብለው ያስተናገዱ ሀገራትን ተቃወመ
የጦሩ አዛዥ ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በሀገራቱ ላይ እርምጃ ልንወስድ እንችላለን ሲሉም ተደምጠዋል
ጀነራል ዳጋሎ በቅርቡ በኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ እና ጂቡቲ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል
የሱዳን ጦር መሪው አብዱልፈታህ አልቡርሃን ተፋላሚያቸውን ጀነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ ተቀብለው ያስተናገዷቸውን ሀገራት አጥብቀው ተቃውመዋል።
ሱዳን ነጻነቷን ያወጀችበት 68ኛ አመት ሲከበር ነው አልቡርሃን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል መሪውን የተቀበሉ ሀገራትን የተቹት።
ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ዘጠኝ ወራት ካስቆጠረው ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
አልቡርሃን ሶስቱ ሀገራት ሄሜቲን ተቀብለው ማስተናገዳቸው የሱዳን ሉአላዊነትን እንደመዳፈር ቆጥረውታል።
“የሱዳን ህዝብን እያጠፋ ያለ ቡድንን መሪ ተቀብሎ ማነጋገር ወንጀሉን እንደመተባበር ይቆጠራል” ያሉት የሱዳን ጦር መሪው፥ ሀገራቱን በስም ባይጠቅሱም ዳጋሎን ያስተናገዱት ሀገራት በስልጣን ላይ ላለው የሱዳን መንግስት እውቅና ለመስጠት የሚቸገሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
የሀገራቱ ድርጊት ጸብ አጫሪ መሆኑን በመጥቀስም የሱዳንን ሉአላዊነት እና ደህንነት ለማረጋገጥ እርምጃ የመውሰድ መብት አለን ብለዋል።
ጀነራል አልቡርሃን ዳጋሎን ባስተናገዱት ሀገራት ላይ ምን አይነት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ግን አልጠቀሱም።
የሱዳን ጦር አልበሽርን ከስልጣን በማንሳቱ ሂደት የተባበረውን የፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) አማጺ ቡድን ብሎ የፈረጀው ሲሆን፥ ከዚህ ቡድን ጋር የሚደረግ ግንኙነት በጥርጣሬ ይመለከተዋል።
ሚሊየኖችን ያፈናቀለው ጦርነት በቀጠለበት ወቅት ተፋላሚዎቹ ጀነራሎችን በየፊናቸው በጎረቤት ሀገራት ጉብኝት እያደረጉ ነው።
ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን አስቀድመው በግብጽ እና በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ተፋላሚዎቹ ጀነራሎች ባደረጓቸው የውጭ ሀገር ጉብኝቶች የሱዳናውያንን ሰቆቃ የሚያስቆም ስምምነት ለመድረስ ቁርጠኝነታቸውን ቢገልጹም እስካሁን ጦርነቱ አልቆመም።
በያዝነው የፈረንጆቹ ጥር ወር ጀነራሎቹን ፊት ለፊት ለማገናኘት ቀጠሮ የያዘችው ጂቡቲም ዳጋሎን ለምን አስተናገድሽ የሚል ወቀሳ ቀርቦባት የድርድሩ ስኬታማነት ከወዲሁ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።