የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀ መንበር አልቡርሃን ወደ ካይሮ አቀኑ
የአልቡርሃን ጉብኝት ከህዳሴው ግድብ ጋር ስለመያያዙ የሚታወቅ ነገር የለም
አልቡርሃን ወደ ካይሮ ያቀኑበት ምክንያት ምን እንደሆነ አልተገለጸም
አልቡርሃን ወደ ካይሮ ያቀኑበት ምክንያት ምን እንደሆነ አልተገለጸም
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀ መንበር ልፍተናንት ጀነራል አብዱል አልፋታህ አል ቡርሃን የአንድ ቀን ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ግብጽ ተጉዘዋል፡፡
ሊቀመንበሩ ወደ ካይሮ ያቀኑት በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ባቀረቡላቸው ግብዣ መሰረት መሆኑን የሱዳን ዜና አገልግሎት ሱና ዘግቧል፡፡
በጉብኝቱ የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ኦማር ጋማር ኤደን እንዲሁም የደህንነት አገልግሎት ኃላፊው ሜጀር ጀነራል ጃማል አብዱል ማጅድ እና ሌሎችም ተካተዋል፡፡
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ ካይሮ ያቀኑበት ምክንያት ምን እንደሆነ በዜና ምንጩ አልተገለጸም፡፡
ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን የሚያደርጉት የሶስትዮሽ የግድቡ ድርድር ዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል፡፡
የአልቡርሃን ጉብኝት ከህዳሴው ግድብ ጋር ስለመያያዙ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
በአሜሪካና በአለም ባንክ አደራዳሪነት ሲካሄደ የነበረው የግድቡ ድርድር በኢትዮጵያ ተቃውሞ ከቋረጠ በኋላ ድርድሩን የአፍሪካ ህብረት እንዲመራው ተስማምተዋል፡፡ ድርደሩ በአፍሪካ ህብረት እየተመራ ይገኛል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክና ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኒታኒያሁ በነበራቸው ንግግር ኢትዮጵያ ስምምነት አቋርጣለች፤ ግብጽ “ግድቡን ታፈነዳዋለች” የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር፡፡
የፕሬዘዳነቱ አስተያየት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ አስከትሎ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር ጠርተው ማብራሪያ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡