ሱዳን ለናይሮቢ እና ዳሬ ሰላም የሽብር ጥቃት ተጎጂዎች ለመክፈል የተስማማችውን ካሳ መክፈሏ ተገልጿል
ሱዳን ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ ሀገሮች ዝርዝር እንድትወጣ ትራምፕ ፈረሙ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሱዳንን ከአሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ የማስወገዱን ውሳኔ በይፋ ፈረሙ፡፡
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ነው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ሱዳንን ለመሰረዝ ውሳኔውን በይፋ መፈረማቸውን በዛሬው ዕለት የገለጸው፡፡
ምክር ቤቱ በይፋዊ የትዊተር አድራሻው ባወጣው መግለጫ “የዛሬው ቀን ለሱዳን ታሪካዊ ነው” ብሏል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ሱዳንን የማስወጣት ዓላማ እንዳላቸው ኋይት ሀውስም ዛሬ አርብ ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. አስታውቋል ፡፡
ፕሬዝዳንት ይህንን ሀሳባቸውን ለኮንግረሱም ማጋራታቸውን ነው የኋይት ሀውስ መግለጫ የሚያመለክተው፡፡
እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ተግባራዊ የሚሆነው በታንዛኒያ እና ኬንያ በሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች በተፈጸመው የሽብር ጥቃት ከተጎዱ ግለሰቦች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮችን ለመፍታት በቅርቡ መስማማቷን ተከትሎ እንደሆነም መግለጫው አስታውሷል፡፡
መግለጫው ሱዳን ትናንት ሀሙስ እለት 335 ሚሊዮን ዶላር ወደተጎጂዎች አካውንት ማስተላለፏንም አረጋግጧል፡፡
ፕሬዘዳንት ትራምፕ በቅርቡ በትዊተር ገጻቸው በጻፉት መልዕክት ሱዳን የካሳ ክፍያውን እንደፈጸመች ሽብርን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ስሟ ይሰረዛል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ከ20 ዓመታት በፊት በታንዛኒያና በኬንያ በሚኘኑት የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ በደረሰው ጥቃት በኤምባሲዎቹ ሲሰሩ የነበሩ አሜሪካውያን መሞታቸውን ተከትሎ አሜሪካ ለጥቃቱ ሱዳንን ተጠያቂ አድርጋ ቆይታለች፡፡