የሱዳን የውጭና የውሃ ሚኒስትሮች ግድቡን በሚመለከተው የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ይሳተፋሉ ተባለ
ምክር ቤቱ በህዳሴው ግድብ ላይ የሶስትዮሽ ውይይቱን ከማበረታታት ውጭ እምብዛም ሊያደርግ የሚችለው ነገር እንደሌለ የም/ቤቱ ወሩ ፕሬዝዳንት መናገራቸው ይታወሳል
የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት የፊታችን ሀሙስ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል
በሚቀጥለው ሳምንት ይካሄዳል በተባለው የጸጥታው ምክር ቤት በህዳሴው ግድብ ላይ በሚያደርገው ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ የሱዳን ባለስልጣናት ወደ ኒዮርክ እንደሚያቀኑ ተገለጸ።
የጸጥታው ምክር ቤት የአረብ ሊግ፣ ሱዳን እና ግብጽ በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጣልቃ እንዲገባ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ምክር ቤቱ በትናንትናው ዕለት የወሩን አጀንዳ በወቅቱ የምክር ቤቱ ፕሬዘዳንት የፈረንሳይ አምባሳደር በኩል አስታዋውቋል።
በመንግስታቱ ድርጅት የፈረንሳይ አምባሳደር ኒኮላስ ደ ሪቬሪ የወሩን አጀንዳ ይፋ ካደረጉ በኋላ ከጋዜጠኞች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል የህዳሴው ግድብ አንዱ ነበር።
የጸጥታው ምክር ቤት በኢትይጵያ ህዳሴ ግድብ አለመግባባት ዙሪያ አገራቱ ወደ ውይይት እንዲመለሱ ከማድረግ ባለፈ እምብዛም ሊያደርግ የሚችለው ነገር እንደሌለ መናገራቸው ይታወሳል።
ምክር ቤቱም በሚቀጥለው ሳምንት በዚህ ዙሪያ ሊሰበሰብ ይችላል የተባለ ሲሆን አሁን ላይ በወጡ መረጃዎች መሰረት ምክር ቤቱ የፊታችን ሀሙስ ይሰበሰባል ተብሏል።
አልአይን አረብኛ ከካርቱም እንደዘገበው ከሆነ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሬም አልሳዲቅ እና የውሃ እና መስኖ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ያሲር አባስ በዚህ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኒዮርክ ይጓዛሉ።
መሪዎቹ ወደ አሜሪካ የሚጓዙት የጸጥታው ምክር ቤት ግድቡ ያደርስብናል ያሉትን ሀሳብ ለማስረዳት ነው።
ኢትዮጵያ ሁለቱ አገራትን ጨምሮ በዓረብ ሊግ ግድቡ የወንዙ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን የውሃ ድርሻ ስለሚጎዳ ተመድ ጣልቃ ይግባ በሚል ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።
ግድቡ በወንዙ ላይ ፍትሀዊ ጥቅምን ከማስጠበቁ ባለፈ ግብጽ እና ሱዳን አመቱን ሙሉ ያልተቆራረጠ ውሃ እንዲደርሳቸው ያደርጋል ብላለች ኢትዮጵያ።
በግድቡ ዙሪያ ያሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሚደረገው ውይይት ብቸኛው መፍትሄ ነውም ስትል ኢትዮጵያ አስታውቃለች።