የዐረብ ሊግ የፀጥታው ም/ቤት በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ እንዲሰበሰብ ጠየቀ
የዐረብ ሊግ በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት እየተካሄደ ያለው የህዳሴ ግድብ ድርድር አዝጋሚ ነው ብሎታል
የዐረብ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ መቀመጥ ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ አይከታትም - ዶ/ር አረጋዊ በርሄ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ባለችው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ስንብሰባ እንዲያደርግ የዐረብ ሊግ ጠየቀ።
የሊጉ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባደረጉት ሰብሰባ የሁሉንም አካላት ፍላጎት የሚያሳካ አስገዳጅ ስምምነት ላይ መደረስ እንዳለበት አንስተዋል።
የዐረብ ሊግ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት እየተካሄደ ያለውን ድርድር አዝጋሚ ነው ሲል ገልጾታል።
ሚኒስትሮቹ በኳታር መዲና ዶኃ ባደረጉት ስብሰባ በአፍሪካ ሕብረት ስር እየተካሄደ ያለው ድርድር አዝጋሚ በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በግድቡ ዙሪያ ስብሰባ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የሊጉ ዋና ፀሀፊ አህመድ አብዱል ጌት እንዳሉት የግብፅ እና የሱዳን የውሃ ደህንነት ጉዳይ የዐረብ ሀገራት ደህንነት አካል መሆኑን መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።
የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የዐረብ ሊግ ለሱዳን እና ለግብፅ ድጋፍ እንዳለውም ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል።
የዐረብ ሊግ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባን አልጄሪያ እንደምታዘጋጅ ተገልጿል።
የዐረብ ሊግ ስብሰባን በተመለከተ አል ዐይን አማርኛ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) አነጋግሯል።
ዳይሬክተሩ፤ ግብፅ እና ሱዳን ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት አቤቱታ ማቅረባቸው እና የዐረብ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ መቀመጥ ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ እንደማይከታትም ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ ከየትኛውም በኩል ለሚመጣ ዓለም አቀፍ ጫና እንደማትንበረከክም ገልጸዋል።
የወቅቱ የዐረብ ሊግ ዋና ጸሐፊ አህመድ አቡል ጌት ከአውሮፓውያኑ 2004 እስከ 2011 ድረስ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ።
ከ2016 ጀምሮ የዐረብ ሊግ ጸሐፊነትን የተረከቡት አቡል ጌት ባለፈው መጋቢት 2021 በድጋሚ የሊጉ ዋና ጸሐፊ ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።