ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ላለው የድንበር ውዝግብ ለሰላማዊ መፍትሄ ዝግጁ መሆኗን ገለጸች
ሱዳንን ለጦርነት የሚገፋፉ ኃይሎች በቅኝ ግዛት አገዛዝ መንፈስ የሚያይዋት መሆናቸውን ኢትዮጵያ ገልጻለች
የሱዳን የደህንነትና መከላከያ ም/ቤት ከኢትዮጵያ ጋር ባለው የድንበር ውዝግብ ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጓል
የሱዳን የደህንነትና መከላከያ ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት ከኢትዮጵያ ጋር ባለው የድንበር ውዝግብ ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጓል፡፡ በሀገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌ/ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን መሪነት በተካሔደው ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎች መተላለፋቸው ተገልጿል፡፡ ይሁንና ስለውሳኔዎቹ በግልጽ የተባለ ነገር የለም፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግጭት በተመለከተ ፣ "አል ፋሻቃ አካባቢ የሱዳን ጦር የሀገሪቱን ድንበር ለማስከበር እና ለመከላከል የወሰደውን እርምጃ የደህንነትና መከላከያ ምክር ቤቱ ማድነቁን" የመከላከያ ሚኒስትሩ ጄኔራል ያሲን ኢብራሂም ተናግረዋል፡፡
አንድ የሱዳን ባለሥልጣን ማክሰኞ ታህሣሥ 20 ቀን 2013 ዓ.ም ከአል አረብያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ላለው የድንበር ውጥረት ሰላማዊ መፍትሄዎችን እንደምትቀበል አስታውቀዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ጁማህ ኪንዳ እንደተናገሩት ሀገራቸው "ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም ትፈልጋለች ፣ ግን ድንበሯን ታስከብራለች" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ኪንዳ “የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች በድንበር ላይ የተደረገው ውጊያ እንዲባባስ ምክንያት ሆነዋል” ሲል የከሰሰ ሲሆን “የሱዳን ጦር ምላሽ መስጠት ነበረበት” ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ተይዞብኝ ቆይቷል ካለችው ቦታ እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን በኃይል አስመልሻለሁ ያለችው ሱዳን ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስናት የአል ፋሻቃ አካባቢ ከፍተኛ ጦር ማሰማራቷ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ም/ጠ/ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፣ የሱዳን ጦር ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከጀመረች ከ 6 ቀናት በኋላ ከጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት መክፈቱን እና በዚህም የንጹሃንን ሞት ጨምሮ በርካታ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡
ሱዳንን ለጦርነት የሚገፋፏት አካላት "ሀገሪቱን በቅኝ አገዛዝ መንፈስ የሚያይዋት ፣ ከዚህ ቀደምም ከቅኝ ገዢዋ ጋር ሆነው ሲያስተዳድሯት የነበሩ ፣ አሁንም የሱዳንን ሰፊ መሬት የያዙ እና የሱዳንን ህዝብ እንደሰው የማያዩ ናቸው" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በትናንትናው ዕለት ተናግረዋል፡፡ እነዚህን አካላት "እኔ መናገር አልፈልግም እናንተው ታውቋቸዋላችሁ" ያሉት ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ይሁንና የተወሰኑ የሱዳን ባለሥልጣናትም ጸብ አጫሪ መግለጫ በመስጠት ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ በድርጊቱ ተሳትፎ እንዳላቸው አንስተዋል፡፡ ሆኖም "ኢትዮጵያ እነዚህ አካላት በከፈቱላት በር እንደማትገባ" እና ከሱዳን ጋር ያላትን ወዳጅነት እንደምትንከባከብ ገልጸዋል፡፡ አካባቢውን ማተራመስ የሚፈልጉ ኃይሎች "በሱዳን በኩል ባይሳካላቸው እንኳን ከሌሎች ጎረቤቶቻችን ጋር ሊያጋጩን ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም" ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተፈጠረውን ክስተት በማስመልከት በሰጡት መግለጫ በሁለቱ ሀገራት መካከል ጦርነት እንዲፈጠር የሚፈልጉ የውጭ ሀይሎች መኖራቸውን አንስተው ፣ ሰሞኑን በተፈጠረው ክስተት የኢትዮጵያና ሱዳን ግንኑነት እንደማይቋረጥ እንዲሁም ችግሩን በሰላም ለመፍታት ኢትዮጵያ ሙሉ ዝግጁነት እንዳላት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡