የፌደራል መንግስት ከሱዳን ጦር ወረራ ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን የህግ ማስከበር እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ
እስከ 200 በሚደርሱ አርሶ አደሮች ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንም ነው አስተዳደሩ የገለጸው
በወረራው ከ1 ቢሊዬን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ተዘርፏል ተቃጥሏልም ያለው የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደር ከ1 ሺ 750 የሚልቁ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አስታውቋል
የሱዳን ጦር በኢትዮጵያ ሰራዊት ሲጠበቁ የነበሩ ቀጣናዎችን እና ካምፖችን ተሻግሮ በመግባት ከፍተኛ ጥፋት በመፈጸም ላይ መሆኑን በአማራ ክልል የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ጥፋቱ የጸጥታ ኃይላችን የህወሓትን የጥፋት ተልዕኮ ለመንቀሳቀስ በማሰብ ለግዳጅ ሲንቀሳቀስ መፈጸም የጀመረ ነው ያለው አስተዳደሩ በአንዳንድ የሰራዊቱ አመራር እና የሌላ ተልእኮ ሴራ ፈፃሚ አካላት በዳግም ከሀዲ ቡድን ዱላ አቀባይነት የሚፈጸም መሆኑን አስታውቋል።
ከጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ማለትም እስከ ታህሳስ 18 ቀን 2013 ዓ/ም ድረስ ከ180 እስከ 200 የሚደርሱ የዞናችን አርሶ አደሮች የእርሻ ካምፖች ተወረዋል ተቃጥለዋልም ያሉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ባልተለመደ ሁኔታ በርካታ መካናይዝድ ጦር በማዝመት በሞርተር፣ በዙ 23 እና በመድፍ ቀጠናውን በማወክ በተስፋፊነት ስሜት በርካታ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ብለዋል።
አስተዳዳሪው ሁኔታውን የተመለከተ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በመግለጫቸው ጦሩ ለዘመናት በአርሶ አደሮቻችን ካምፕ የተከማቹ የእርሻ መሳሪያዎችን፣ ሰብል እና እንስሳትን ሳይቀር ከመዝረፍና ከማቃጠል ባሻገር ዜጎችን እያሠረና እያንገላታ ይገኛል ብለዋል።
በጉዳቱም ከ1 ቢሊዬን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ተዘርፏል በቃጠሎ ወድሟልም ነው አቶ ደሳለኝ በመግለጫቸው ያሉት።
ከ450 እስከ 500 ከዚያ በላይም የሚሆኑ አባወራ እና እማወራዎች በጥቅሉ ከ1 ሺ 750 በላይ የሰላም በር ቀበሌ ህዝቦች ተፈናቅለዋል፤ሰፈራቸው እየተቃጠለ ይገኛልም ብለዋል።
“የዞኑ ህዝብ ወንድም ለሆነው የሱዳን ህዝብ እና መንግስት ካለው ክብር፣ አብሮ ለመኖር እና ለሰላም ካለው ፍላጎት የተነሳ መንግስትና ህዝብ ያሉትን የሰላም አማራጮች ሁሉ አሟጦ የመጠቀም ጥረቱን በመረዳት በሆደ ሰፊነት ነገሮችን እየተመለከተ ነው” ነው የዋና አስተዳዳሪው መግለጫ የሚለው።
አስተዳዳሪው በቅርብ የሚገኙ የአካባቢው ከተሞች አሁንም በስጋት ላይ መሆናቸውንም አልሸሸጉም ።
በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት በተለይም ደግሞ የፌደራሉ መንግስት ሁኔታውን ተረድቶ የሰላም አማራጭ በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የማይመጣ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት እየደረሰ ያለውን ጉዳት ሊመለከት ይገባል ብለዋል፡፡
በተጀመረው ሰላማዊ የድርድር አማራጭ አለበለዚያም አስፈላጊው ህግ የማስከበር እርምጃ ተወስዶ የዞኑ ህዝብ ከተጋረጠበት የደህንነት ስጋት ወጥቶ ወደ ቀደመ ሰላሙ እና ልማቱ እንዲመለስ አስፈላጊው አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል።