አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን በቀጣይነት እንድትሞላ እንደማትፈቅድ ሱዳን ገለጸች
ሱዳን አለመግባባቱን ለመፍታት ኃይል የመጠቀም ፍላጎት እንደሌላት የሀገሪቱ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቋል
ቀጣዩ ሙሌት ያለስምምነት ከተከናወነ በሱዳን ላይ የደህንነት ስጋት እንደሚደቅን የዉሃ ሚኒስትሩ ገልጸዋል
ግድብ የዉሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ ላይ አስገዳጅ ስምምነት እስካልተደረሰ ድረስ ፣ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር የዉሃ ሙሌት እንድታከናውን አልፈቅድም ስትል ሱዳን አስታውቃለች፡፡
የሱዳን የመስኖና የዉሃ ሀብት ሚኒስትር ያሰር አባስ ፣ ሁለተኛው ዙር ሙሌት ያለስምምነት ከተከናወነ በሱዳን ደህንነት ላይ ስጋት ይደቅናል ብለዋል፡፡
የመስኖና የውሃ ሚኒስትሩ ያሰር አባስ እና ተጠባባቂ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኦማር ቀመረዲን ትናንት ዕሁድ ምሽት በሱዳን ቴሌቪዥን ቀርበው እንዳሉት ፣ ሀገራቸው አለመግባባቱን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ውጭ ወታደራዊ እርምጃ የመውሰድ ፍላጎት የላትም፡፡
ሱዳን ከሕዳሴው ግድብ በታች በሚገኙ ትንንሽ ግድቦቿ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከሕዳሴው ግድብ ሙሌት እና አለቃቀቅ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርብ ትብብር መስራት የሚቻልበት ሰምምነት ላይ መድረስ ትፈልጋለች፡፡ ከዚህ ውጭ በግድቡ ግንባታ ላይ ቅሬታ እንደሌላት እና ግድቡ ሱዳንን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የሀገሪቱ መንግስት በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡
ምንም እንኳን በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ላለፉት 10 ዓመታት በኢትዮጵያ ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል ድርድሮች ቢካሔዱም እስካሁን የተሟላ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም፡፡
የአፍሪካ የውሃ እና የወንዝ ባለሙያዎች በድርድሩ ላይ የላቀ ሚና እንዲኖራቸው ሱዳን ያቀረበችው ምክረ ሀሳብ በሁለቱ ሀገራት ተቀባይነት አለማግኘቱን ተከትሎ ሱዳን ባለፈው ወር ራሷን ከድርድሩ ማውጣቷ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ካርቱም በቅርቡ ወደ ድርድሩ ልትመለስ እንደምትችል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቀመረዲን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣዩ ክረምት ተጨማሪ 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለመያዝ አቅዳ እየሰራች ነው፡፡ ሱዳን የደህንነት ስጋት ይደቅንብኛል ያለችው የቀጣዩ ሙሌት ጊዜ ያለስምምነት ከደረሰ ፣ አለመግባባቱን በአሸማጋዮች የመፍታት ፍላጎት እንዳላት የገለጹት የሀገሪቱ የዉሃ እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ፣ ሀገራቸው ችግሩን ለመፍታት ወታደራዊ ኃይል የመጠቀም ፍላጎት እንደሌላትም ነው የተናገሩት፡፡ ተጠባባቂ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኦማር ቀመረዲን “ኃይል መጠቀም በሱዳን ዘንድ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል፡፡
የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል ሲሲም አለመግባባቱ በኃይል ሳይሆን በድርድር ብቻ እንደሚፈታ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
ልዩነቱን ለመፍታት ፣ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ከኢትዮጵያ እና ከግብጽ መሪዎች ጋር በተከታታይ ንግግር ሲያደርጉ መቆየታቸውን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በሶስቱ ሀገራት መካከል ቀጣዩ ድርድር መች እንደሚካሔድ ተቆርጦ የተቀመጠ ቀን የለም፡፡
የዘገባው ምንጭ ዘ ናሺናል ነው፡፡