የሱዳን ኃይሎች ጥምረት "ጦርነት በማስቆም ጉዳይ" ላይ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው
ጥምረቱ የጦርነቱን መቀጠል የሚቃወሙ የሲቪል እና የፖለቲካ ኃይሎችን እንዲሁም የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያካሄዱ አካላት ስብስብ ነው
ስብሰባው በሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እና ጦርነቱን በማቆም ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሏል
በቀድሞው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የሚመራው 'ኮኦርዲኔሽን ኦፍ ሲቪል ዲሞክራቲክ ፎርስስ' የተባለው የሱዳን ኃይሎች ጥምረት በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ውይይት ጀምሯል።
በዚህ ስብሰባ ከ30 በላይ ሀገራት እና ከ18 ግዛቶች የተውጣጡ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን በሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እና ጦርነቱን በማቆም ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሏል።
እስከ ግንቦት 30 ድረስ እንደሚቆይ መርሃግብር በተያዘለት በዚህ ስብሰባ አብደላ ሀምዶክም ተገኝተዋል።
ጥምረቱ የጦርነቱን መቀጠል የሚቃወሙ የሲቪል እና የፖለቲካ ኃይሎችን እንዲሁም የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያካሄዱ አካላትን የያዘ ስብስብ ነው።
በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ውስጥ ገለልተኛ እንደሆነ የሚገልጸው ጥምረቱ የተቋቋመው ጥቅምት 2023 ነበር።
የጥምረቱ ቃል አቀባይ በክሪ አል ጃክ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በስብሰባው ከ600 በላይ ተሳታፊዎች እንደተገኙ ተናግረዋል። ቃል አቀባዩ እንደገለጹት የተወሰኑት ተሳታፊዎች ሱዳን ውስጥ ከሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች እንዳይሳተፉ ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል።
ቃል አቀባዩ አል ጃክ ጥምረቱ ሱዳናውያን የሚስማሙት አንድነቷ የተጠበቀ ሀገር እንዲኖር ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።
ሱዳንን ሶሰት አስርት አመታት ለሚጠቃ ጊዜ ሲያስተዳድሯት የነበሩት ኦመር ሀሰን አልበሽር በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን ከወደቁ በኋላ ሱዳን ቀውስ ውስጥ ገብታልች።
ከአልበሽር ውድቀት በኋላ በተቋቋመው ጊዜያዊ የሲቪል አስተዳደር ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አብደላ ሀምዶክ መፈንቅለ መንግስት ተካሂዶባቸው ከስልጣን ወርደዋል።
አብደላ ሀምዶክ ሀገሪቱ ከወታደራዊ ስልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደር እንድትሸጋገር የሚያስችሉ ሂደቶችን እንዲከውኑ ነበር የተሾሙት።
ነገርግን ሀምዶክም ከመፈንቅለ መንግስት አልተረፉም።
የሱዳን የጦር መሪዎችን በሀምዶክ ላይ መፈንቅለ መንግስት በማድረግ አጠቃላይ የሀገሪቱን ስልጣን ሊቆጣጠሩ ችለዋል። ይህ ግን የሱዳን ቀውስ መጨረሻ አልነበረም።
መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ በተባበሩት የሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አል ቡርሃን እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ መካከል ባለፈው ሚያዝያ ወር ጦርነት ተቀሰቀሰ። በዚህ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን የተገደሉ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።