የህወሓት ኃይሎች ለሱዳን ጦር ቅጥረኛ ሆነው እየተዋጉ ነው መባሉን ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስተባበለ
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በትናትናው እለት ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች ከሱዳን ጦር እና ተባባሪ ሚሊሻዎች ጋር ሆነው እየተዋጉት እንደሆነ ማረጋገጡን ገልጿል
የህወሓት ኃይሎች ከሱዳን ጦር ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ ነው የሚለውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች "መሰረተቢስ ክስ" በጽኑ እንደሚያወግዝ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ገልጿል
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዛሬ ባወጣው መግለጫ "የህወሓት ኃይሎች" ከሱዳን ጦር ጎን በቅጥረኝነት ተሰልፈው ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጋር እየተዋጉ ነው መባሉን አስተባብሏል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህን ያለው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ባለፈው ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች ከሱዳን ጦር እና ተባባሪ ሚሊሻዎች ጋር ሆነው እየተዋጉት እንደሆነ ማረጋገጡን መግለጹን ተከትሎ ነው።
የሱዳን ጦርነት ከተጀመረበት ከሚያዝያ 2023 ወዲህ የሱዳን ጦር የውጭ ቅጥረኞችን እርዳታ እየፈለገ ነው የሚል ክስ ያቀረበው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር፣ በጦርነት ወቅት ተገድለው የተገኙ ቅጥረኞችን መመዝገቡን ጠቅሷል።
የህወሓት ኃይሎች ከሱዳን ጦር ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ ነው የሚለውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች "መሰረተቢስ ክስ" በጽኑ እንደሚያወግዝ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ገልጿል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደገለጸው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ይህን ክስ ያቀረበው፣ በሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያለቁበትን የእርስበርስ ጦርነት አለምአቀፋዊ ይዘት በማላበስ በሱዳን ጦር ላይ ለሚያደርገው ዘመቻ ድጋፍ ለማሰባሰብ ነው።
ህወሓት የፖለቲካ ፓርቲ በመሆኑ ታጣቂ ክንፍ እንደሌለው በግልጽ የሚታወቅ ነው ያለው ጊዜያዊ አስተዳዳሩ ክሱን ውድቅ አድርጎታል።
በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በፌዴራል መንግስታት እና በህወሓት መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ መጠለያ ፍለጋ ወደ ሱዳን የተሰደዱ የትግራይ ተወላጆች መኖራቸውን እና በችግር ውስጥ ያለው የሱዳን መንግስትም እርዳታ እንዳደረገላቸው የጠቀሰው የጊዜያዊ አስተዳደሩ መግለጫ፣ "ትግራይ በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የምትገባበት ምክንያት የለም" ብሏል።
በጦርነቱ ወቅት "ትግራይ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ባልሆነ የውጭ ኃይሎች ጣልቃገብነት" ከፍተኛ መከራ አስተናግዳለች፤ በሱዳን ጦርነትም የውጭ ኃይሎች ተሳትፎ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ የትግራይ ህዝብ ይረዳል ብሏል ጊዜያዊ አስተዳደሩ።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ከግጭት አባባሽ መግለጫዎች እንዲታቀቡ እና ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲሹ ጠይቋል።
የሱዳን ጦር፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ባቀረበው ክስ ላይ ምላሽ አልሰጠም።
በሱዳን መፈንቅለ መንግስት ያደረጉት ሁለት ጀነራሎች በሚመሩት ጦር መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በሺዎች እንዲገደሉ እና ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ሱዳናውያን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓቸዋል።