የሱዳን ጦር አዛዥ ጀነራል አልቡርሀን ተመድን "ቀውስ በማባባስ" ወቀሱ
ጀነራሉ በሱዳን የተመድ ልዩ ልዑክ የሆኑት ቮከር ፐርትስን ወደ ካርቱም እንዳይልክ አስጠንቅቀዋል
በሱዳን የጸጥታ ሀይሎች መካከል የተጀመረው ጦርነት 48ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል
የሱዳን ጦር አዛዥ ጀነራል አልቡርሀን ተመድን "ቀውስ በማባባስ" ወቀሱ።
በጎረቤት ሀገር ሱዳን በሀገሪቱ ብሔራዊ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች መካከል የተጀመረው ጦርነት 48ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል።
በዚህ ጦርነት እስካሁን ከአንድ ሺህ በላይ ንጹሀን ሲገደሉ፣ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ሱዳናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።
በሪያድ ከተማ በሳውዲ አረቢያ እና አሜሪካ አደራዳሪነት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በተደጋጋሚ ወደ ስምምነት ቢመጡም ስምምንቶቹ በመጣስ ላይ ይገኛሉ።
ከሪያዱ ድርድር ራሱን ያገለለው የሱዳን ብሔራዊ ጦር አዛዥ ጀነራል አልቡርሀን ተመድን በቀውስ አባባሽነት ከሰዋል።
በሱዳን የተመድ ተወካይ የሆኑት ቮከር ፐርትስ በካርቱም በተፈጠረው ቀውስ አወንታዊ ሚናን ከመጫወት ይልቅ አባባሽ ሚና ነበራቸው በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ተወካዩ የሱዳን ብሔራዊ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች በካርቱም ለተፈጠረው ቀውስ እኩል ሚና አላቸው በሚል ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አስተያየት ሰጥተዋል በሚል በጀነራል አልቡርሀን ክስ ቀርቦባቸዋል።
ጀነራል አልቡርሀን ለተመድ በጻፉት ደብዳቤ በፐርትዝ ምይክ ሌላ ሰው እንዲመደብላቸው መጠየቃቸውም ተገልጿል።
ይህ በዚህ እንዳለ ተመድን ጨምሮ በርካታ ዲፕሎማቶች እና ተቋማት ለፐርትዝ ድጋፋቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።