የሱዳን ጦር ከጂዳው ድርድር መውጣቱ ተነገረ
ጦሩ ማረጋገጫ ባይሰጥም የሱዳን ዲፕሎማቶችን የጠቀሱ መገናኛ ብዙሃን ጦሩ ከጂዳው ድርድር ራሱን ማግለሉን እየገለጹ ነው
በካርቱምና ኦምዱርማን ዳግም ግጭት ማገርሸቱ ተነግሯል
የሱዳን ጦር በሳኡዲ እና አሜሪካ ሸምጋይነት ከሚካሄደው ድርድር መውጣቱ ተነገረ።
ጦሩ እስካሁን ማረጋገጫ ባይሰጥም የሱዳን ዲፕሎማቶችን የጠቀሰው ሬውተርስ ጦሩ ከጂዳው ድርድር ራሱን ማግለሉን ዘግቧል።
የሱዳን ጦር ሁለት የተጣሱ የተኩስ ማቆም ስምምነቶች ከተደረሱበት የጂዳው ድርድር መውጣቱ ስድስተኛ ሳምንቱን የያዘው ጦርነት ዳግም እንዳያገረሽ ስጋት ፈጥሯል።
በትናንትናው እለትም በደቡባዊ ካርቱምና ኦምዱርማን ከባድ ውጊያ ስለመካሄዱ ነው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዘገበው።
የሱዳን ጦር መሪው ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ትናንት ወታደሮቻቸውን ሲጎበኙ ያደረጉት ንግግርም ጦርነቱ ቀጣይነቱን ያመላከተ ነበር።
የሱዳን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ በአደባባይ የታዩት ጀነራል አልቡርሃን “ጦሩ ሙሉ የጦር መሳሪያውን አልተጠቀመም፤ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በድርጊቱ ከገፋበት ግን በሙሉ ትጥቁ መዋጋት ይጀምራል” ማለታቸው የሚታወስ ነው።
“ድል እስክንጎናጸፍና ሀገራችን በአማጺያን እጅ አለመውደቋን እስከምናረጋግጥ ድረስ እንታገላለን” ማለታቸውም ከጂዳው ድርድር የመውጣታቸው ምልክት ተደርጎ እየተጠቀሰ ነው።
ጦሩ ሬውተርስ ከምንጮቼ አገኘውት ያለውን መረጃ እስካሁን ባያረጋግጥም የትናንቱ ጉብኝታቸውና ንግግራቸው ውጊያው መቀጠሉ እንደማይቀር ያሳያል ተብሏል።
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በጂዳ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት የንጹሃንን ንብረት መዝረፊያ እና ንጹሃንን ማሰቃያ አድርጎታል ሲሉም ኮንነዋል።
ተሻግሮ በማሰቃየትና በግድያ ላይ ተሰማርቷል ማለታቸውንም ሱዳን ኒውስ አስነብቧል።
አርኤስኤፍ በበኩሉ የሱዳን ጦር የተደረሱ የተኩስ ማቆም ስምምነቶችን በመጣስ የአየር ድብደባውን መቀጠሉን በመግለጽ፥ በጂዳ ለተደረሰው ስምምነት ተፈጻሚነት ቁርጠኛ ነኝ የሚል መግለጫ አውጥቷል።
ይሁን እንጂ በሚሊየኖች ለሚቆጠሩ ሱዳናውያን የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የተፈረመውን የመርህ ስምምነት በመጣሱ ረገድ ሁለቱም ሃይላት ተጠያቂ ናቸው።
በሱዳን ከ46 ቀናት በፊት የተጀመረው የጀነራሎቹ ጦርነት 1 ሺህ የሚጠጉ ንጹሃንን ህይወት ቀጥፎ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ሱዳናውያንን ከቀያቸው አፈናቅሏል።