አሜሪካ ከሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ባላቸው ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች
ተፋላሚ ኃይሎቹ በአሜሪካ እና በሳኡዲ አረቢያ አደራዳሪነት በጂዳ ለድርድር ተቀምጠው የነበረ ቢሆንም የመጣ ለውጥ የለም
አሜሪካ በሱዳን ያለውን ግጭት እያባባሱ ነው ስትል በከሰሰቻቸው ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጥላለች
በሱዳን፣ በሱዳን ጦር እና በጀነራል ሀምዳን ደጋሎ በሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
አሜሪካ በሱዳን ያለውን ግጭት እያባባሱ ነው ስትል በከሰሰቻቸው ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
አሜሪካ ይህን እርምጃ የወሰደችው በተለያየ ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት እየተፈራረሙ ተግባራዊ ማድረግ ያልቻሉት የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ተኩስ እንዲያቆሙ ለማድረግ ነው ተብሏል።
የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር ግዘፉን የመከላከያ ኢንተርፕራይዝ ጨምሮ ከሱዳን ጦር ጋር ግንኙነት ባላቸው ኩባንያዎች እና አንድ በወረቅ ማዕድን ማውጣት የተሰመራ ኩባንያን ጨምሮ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር ግንኙነት ባላቸው ሁለት ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ መጣሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሁለቱ ተፋላሚዎች ግጭት የማያቆሙ ከሆነ አሜሪካ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ልትጥል እንደምትችል አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአሜሪካ ባለስልጣን ተናግረዋል።
ባለስለጣኑ እንዳሉት ማዕቀቡ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መሳሪያ እንዳያገኙ የማድረግ አላማ እንዳለው ገልጸዋል።
ተፋላሚ ኃይሎቹ በአሜሪካ እና በሳኡዲ አረቢያ አደራዳሪነት በጂዳ ለድርድር ተቀምጠው የነበረ ቢሆንም የመጣ ለውጥ የለም።
የሱዳን ጦር ከድርድሩ መወጣቱን ማሳወቁን ተከትሎ ጦርነቱ ተባብሶ ቀጥሏል።