በሱዳን እየተባባሰ በመጣው የኑሮ ውድነት ምክንያት ህዝቡ ለተቃውሞ አደባባይ ወጥቷል
የምክርቤቱ ስብሰባ በሉአላዊ የሽግግር ምክርቤቱ ፕሬዘዳንት አልቡርሃን ነበር የተመራው
በፈረንጆቹ 2018 ተከስቶ የነበረው አመጽ ሱዳንን ለሶስት አስርት አመታት ያህል ያስተዳደሯት አልበሽር ከስልጣን እንዲነሱ ምክንያት ሆኖ ነበር
በሱዳን እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት በመቃወም በዋና ከተማዋ ካርቱም ነዋሪዎች መንግስትን ለመቃወም አደባባይ ወጥተዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከሚሄደው የዋጋ ጭማሪ በተጨማሪ ፣ እየተባባሰ የመጣውን የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ የዳቦ እና የነዳጅ ችግሮች ለመቃወም ሰልፎች በተለያዩ የካርቱም አካባቢዎች መካሄድ ከመጀመሩ ዛሬ ሦስተኛ ቀን አስቆጥረዋል፡፡
የአንዳንድ ዋና ዋና መንገዶች የዘጉትና እና ጎማዎች ያቃጠሉት ሰልፈኞቹ በዋጋ ጭማሪ እና በረጅሙ የዳቦ እና የነዳጅ ሰልፍ መማረራቸውን ገልጸዋል፡፡
በካርቱምና በሳሃፋ ግዛት ውስጥ የተቃውሞ ሰልፈኞች ኢኮኖሚያዊ ሁኔታውን ለማውገዝ ወደ ወደብ እና አንዳንድ ዋና ዋና መንገዶች የሚወስዱ በርካታ መንገዶችን በመዝጋት ጎማዎችን አቃጥለዋል ፡፡
በማዕከላዊ ካርቱም ተቃዋሚዎች ሁኔታውን በመቃወም አንዳንድ ዋና መንገዶችም የተዘጉ ሲሆን ትልቁ መንገድ ከካርቱም ለሚገቡ እና ለሚወጡ መኪኖች ዝግ ሆኗል፡፡
በሱዳን በዳቦና በነዳጅ እጥረት ምክንያት በፈረንጆቹ 2018 ተከስቶ የነበረው አመጽ ሱዳን ለሶስት አስርት አመታት ያክል ያስተዳደሯት አልበሽር ከስልጣን እንዲነሱ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል፡፡
የኢኮኖሚ ቀውስ በተጠናከረበትና የሸቀጦች ዋጋ በጨመረበት ወቅት የሱዳን ሉአላዊ ምክርቤትና ካቡኔ ለፈረንጆቹ 2021 የሚሆን በጀት አጽድቋል፡፡ የምክርቤቱ ስብሰባ በሉአላዊ የሽግግር ምክርቤቱ ፕሬዘዳንት አልቡርሃን ነበር የተመራው፡፡
የሱዳን የኢኮኖሚና የፋይናንስ ጉዳዮች ሚኒስትር ሄባ ሙሃመድ አሊ በጀቱ ሱዳን ሽብርን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ከወጣችና ከጁባ የሰላም ስምምነት በኋላ የጸደቀ የመጀመሪያ በጀት ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ እንዳሉት በጀቱ ለማብሰያ ጋዝ፣ለስንዴ፣ለመድኃኒትና ለኤሌክትሪክ ሲቲ ድጎማ እንደሚያካትት ተናግረዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት የነበራት ሱዳን፣ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል “የህግ ማስከበር ዘመቻ” ከጀመረች በኋላ የኢትዮጵን ድንበር በመጣሷ ምክንያት ግንኙነቷ ሻክሯል፡፡