የሱዳን የጸጥታ ኃይሎች የዲሞክራሲ ደጋፊ በሆኑ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ ተጠቀሙ
ተቃዋሚዎቹ እርምጃ የተወሰደባቸው ወደ ሀገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግስት በማቅናት ላይ ሳሉ ነበር ተብሏል
ሰልፈኞቹ በሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ኃይሎች መካከል የተፈረመውን የስምምነት ማዕቀፍ ሲቃወሙ ተደምጠዋል
የሱዳን የጸጥታ ኃይሎች የዲሞክራሲ ደጋፊ በሆኑ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ ተጠቀሙ፡፡
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ዑመር ሐሰን አል-በሽር ከስልጣን የተወገዱበት ህዝብ ማዕበል አራተኛ አመት ለመዘከር እንዲሁም አሁን በስልጣን ያለው ወታደራዊ ኃይል ለመቃወም በሚል በሺዎች ሱዳናውያን የዴሞክራሲ ደጋፊዎች ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
ይሁን እንጅ ከባድ ድባብ በነበረው ሰልፍ ያልተደሰቱት የሱዳን የጸጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎቹ ላይ አስለቃሽ ጭስ በመጠቀምና ተኩስ በመክፈት ሰልፉን እንደበተኑት እየተነገረ ነው፡፡
ሰልፈኞቹ በጸጥታ ኃይሎች እርምጃ የተወሰደባቸው ወደ ሀገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግስት በማቅናት ላይ ሳሉ እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡
ሰልፈኞቹ በቅርቡ በሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ኃይሎች መካከል የተፈረመውን የስምምነት ማዕቀፍ ግልጽነት የጎደለው በማለት ተቃውመውታል፡፡
በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት የተቸረው ስምምነት ፤ ሱዳናውያን በጉዳዩ ላይ ልዩነቶች እንዲያንጸባርቁ ምክንያት ሆኗልም እየተባለ ነው፡፡
አንዳንድ ሱዳናውያን ስምምነቱ መረጋጋት ሊያመጣ ይችላል ሲሉ ሌሎች ደግሞ የወታደራዊውን ኃይል ተሳትፎ ውድቅ ያደርጋሉ።
በሱዳን የዴሞክራሲ አቀንቃኞች ጥምር ኃይል እና ወታደራዊ ኃይሉ መካካል የተፈረመው ስምምነት ሀገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ፣ ለሁለት ዓመታት የሚዘልቅ የሲቪል የሽግግር አስተዳደር እንደሚኖር ተገልጿል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አልባሽር በህዝባዊ ተቃውሞ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ፣ ሱዳን ላለፉት አራት ዓመታት የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ እንደቆየች ይታወቃል።
የአህጉሪቱ ተቋም የአፍሪካ ህብረት፣ የአረብ ሀገራት እንዲሁም ምዕራባውያን በሱዳን ወታደራዊ ኃይል እና በሲቪል አመራሩ መካከል ስምምነት ተደርሶ በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን የተለያዩ ጥረቶች ሲያደረጉ መቆየታቸውም አይዘነጋም፡፡