የሱዳን ፖለቲከኞች ከስምምነት ቢደርሱም ህዝባዊ ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው
የተፈረመው ስምምነት ሀገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል
ተቃዋሚዎቹ፤ "መፈንቅለ መንግስቱን እንዳፈረስን ሁሉ ስምምነቱን እናፈርሳለን" እያሉ ነው
የሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ኃይሎች በሀገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ሽግግር ለመጀመር ያስችላል የተባውን የስምምነት ማዕቀፍ ቢፈራረሙም በሀገሪቱ የሚደረገው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ወታደራዊ እና ሲቪል ፓርቲዎች ሰኞ እለት የሲቪል መንግስት ምስረታ ስምምነት ላይ የደረሱበት ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግስት አቅራቢያን ጨምሮ በበርካታ የካርቱም አካባቢዎች የተቃውሞ ድምጾች ሲያሰሙ መታየታቸው የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
የሱዳን የጸጥታ ኃይሎች በዋና ከተማው የተበተኑ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር ባደረጉት ጥረት አስለቃሽ ጭስ ተጠቅመው መንገዶችን እና ድልድዮችን መዝጋታቸውም ተገልጿል፡፡
በሱዳን ፖለቲከኞች መካካል ተደረሰው ስምምነት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት ቢቸረውም፤ ሱዳናውያን በጉዳዩ ላይ ልዩነቶች እንዲያንጸባርቁ ምክንያት ሆኗል እየተባለ ነው፡፡
አንዳንድ ሱዳናውያን ስምምነቱ መረጋጋት ሊያመጣ ይችላል ሲሉ ሌሎች ደግሞ የወታደራዊውን ኃይል ተሳትፎ ውድቅ ያደርጋሉ።
በካርቱም በተደረገው ሰልፍ ተሳታፊ የሆነው የ22 ዓመቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳፋ ሳሌህ "መፈንቅለ መንግስቱን እንዳፈረስን ሁሉ ስምምነቱን እናፈርሳለን" ሲል ለተደረሰው ስምምነት ያለውን ተቃውሞ ገልጿል፡፡
ፍትህ ለሰማዕታት እንሻለን ወታደርንም አንቀበልም ሲልም አክሏል የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳፋ ሳሌህ፡፡
ሰኞ እለት በሱዳን የዴሞክራሲ አቀንቃኞች ጥምር ኃይል እና ወታደራዊ ኃይሉ መካካል የተፈረመው ስምምነት ሀገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ፣ ለሁለት ዓመታት የሚዘልቅ የሲቪል የሽግግር አስተዳደር እንደሚኖር ተገልጿል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አልባሽር በህዝባዊ ተቃውሞ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ፣ ሱዳን ላለፉት አራት ዓመታት የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ እንደቆየች ይታወቃል።
የአህጉሪቱ ተቋም የአፍሪካ ህብረት፣ የአረብ ሀገራት እንዲሁም ምዕራባውያን በሱዳን ወታደራዊ ኃይል እና በሲቪል አመራሩ መካከል ስምምነት ተደርሶ በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን የተለያዩ ጥረቶች ሲያደረጉ መቆየታቸውንም አይዘነጋም፡፡