የሱዳን መንግስት በተነሳው ተቃውሞ ምክንያት መንግስት እና የግል ስራ እንዲቆም አዟል
ሱዳናውያን ዛሬ ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸውን ተከትሎ በመላው ሀገሪቱ ስራ እንዲዘጋ ውሳኔ ተላለፈ፡፡
የሚያዚያ ወር ሱዳናውያን በሰላማዊ ተቃውሞ መሪዎቻቸው ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁበት ሲሆን ዛሬም ተመሳሳይ ጥያቄ ያነገቡ ሰልፈኞች የካርቱምን ጎዳናዎችን ሞልተዋል፡፡
የሱዳን መንግስት ዛሬ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ምክንያት የመንግስትም ሆነ የግልም ስራ ሙሉ ለሙሉ እንዲቆም ማድረጉ ተገልጿል፡፡ የካርቱም ባለስልጣናት ከሰሞኑ ወደ ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግስት የሚወስዱ መንገዶች እንዲዘጉ የወሰኑ ሲሆን በትምህምርት ቤቶችና በህክምና ተቋማት አቅራቢያ ሰልፍ ማድረግ አይቻልም የሚል መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡
የሀገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች በተለያዩ ቦታዎች ስምሪት ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን ወደ ካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚወስደው መንገድም በከፍተኛ ጥበቃ ስር መሆኑን አስተያየታቸውን ለአል ዐይን የሰጡ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
አውሮፕላን ማረፊያው፣ ወደ ነጭ ዓባይ ድልድይ መግቢያ የሚወስደው መንገድና ወደሌሎች ድልድዮች አካባቢ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሱዳን ሰራዊት እንዳለው ተገልጿል፡፡ ሱዳናውያን በተደጋጋሚ ወደ አደባባይ በመውጣት የፍትህ፤ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቻቸውን እያቀረቡ ናቸው፡፡
የቀድሞው የሱዳን መሪ ኦማር ሃሰን አል በሽር ከስልጣን የተወገዱት ሚያዚያ ወር ላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በሱዳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛን ከሀገሪቱ ሊያባርሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቀው ነበር፡፡
አል-ቡርሃን፤ ልዩ መልዕክተኛው ቮልከር ፔሬዝ “በሱዳን ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን ያቁሙ” ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን ልዩ መልዕክተኛውም ሱዳንን በተመለከተ ሪፖረታቸው ላይ ችግር ካለ ድጋሚ እንደሚመለከቱት ገልጸዋል፡፡